
አዲስ አበባ: ታኅሣሥ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ንግድ ቢሮ “የምርት አቅርቦት ለገበያ ማረጋጋት” በሚል መሪ መልዕክት የዕውቅና መርሐ ግብር አካሂዷል። በመርሐ ግብሩ አምራቾች፣ አቅራቢዎች ነጋዴዎች እንዲኹም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ንግድ ቢሮ ኀላፊ ሀቢባ ሲራጅ በከተማው ጤናማ የንግድ ሥርዓትን በመዘርጋት ገበያውን ለማረጋጋት በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት በ11 ክፍለ ከተሞች የገበያ ማዕከላትን በመገንባት አምራች እና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት ምርትን በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ ማቅረብ መቻሉን አንስተዋል። ማዕከላቱ የሰብል፣ የአትክልት እና ፍራፍሬ፣ የኢንዱስትሪ ብሎም የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች ግብይት የሚካሄድባቸው እንደኾነም ተናግረዋል።
የገበያ ማዕከላቱ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓትን በመዘርጋት ሕገ ወጥ ንግድን ለመቆጣጠር ሚናቸው ላቅ ያለ ሥለመኾኑም ኀላፊዋ ጠቁመዋል። ይህም በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በቀላሉ እንዲሸምቱ በማድረግ የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል የሚያስችል ነው ብለዋል።
እንደ ቢሮ ኀላፊዋ ገለጻ በከተማ አሥተዳደሩ 500ሺህ ነጋዴዎች በንግድ ሥርዓቱ ገብተዋል። በ11 ክፍለ ከተሞች 10 የገበያ ማዕከላት አሉ። ከእነዚህ መካከል አምስቱ የግብርና ምርቶች መሸጫ ማዕከላት ናቸው። በእነዚህ ማዕከላትም 197 የቅዳሜ እና እሑድ ገበያ ማዕከላት ይገኛሉ። የቅዳሜ እና እሑድ ገበያ የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደኾነም አስገንዝበዋል።
የገበያ ማዕከላትን በማስፋት እና ምርትን በብዛት በማቅረብ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም ጠቅሰዋል። ቢሮው ባለፉት ዓመታት ለገበያ መረጋጋቱ ትልቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማት አምራቾች እና አቅራቢዎች ዕውቅና ሰጥቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ንግድ ቢሮ ከአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ጋር የገበያ ትሥሥር ለመፍጠር የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ስለመፈራረማቸውም ነው የተናገሩት።
ሥምምነቱ የምርት አቅርቦት ችግርን የሚፈታ እና የኑሮ ውድነቱን ከማረጋጋት በተጨማሪ የአምራች አርሶ አደሩን፣ አቅራቢ እና ሸማቹን ማኅበረሰብ የበለጠ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው ተብሏል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!