ማኅበረሰቡ የወባ ትንኝ መራቢያ ቦታዎችን የማፋሰስ፣ የማዳፈን እና የማጽዳት ሥራ እንዲሠራ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) አሳሰቡ።

31

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ታኅሣሥ 25/2017 ዓ.ም በክልሉ ሁሉም ወባማ ቀበሌዎች የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የወባ ትንኝ መራቢያ ቦታዎችን የማፋሰስ፣ የማዳፈን እና የማጽዳት ሥራ እንዲሠራ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አሥተባባሪ እና የክልላዊ የወባ መከላከል ግብረ ኀይል ሠብሣቢ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር ) አሳስበዋል።

በአማራ ክልል ከሐምሌ 1/2016 ዓ.ም እስከ ታኅሣሥ አጋማሽ 2017 ዓ. ም ድረስ 3 ሚሊዮን 112 ሺህ 772 ሰዎች የወባ ምርመራ አድርገዋል። ከተመረመሩት ውስጥ 1 ሚሊዮን 315 ሺህ 970 የሚኾኑት የወባ በሽታ ሕሙማን እንደኾኑ አንስተዋል። በተለይም ደግሞ በክልሉ 40 ወረዳዎች የክልሉን 70 በመቶ የወባ ሥርጭት ይሸፍናሉ ተብሏል።

እስከ ታኅሣሥ አጋማሽ ያለው የወባ ሥርጭት ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 64 በመቶ መጨመሩንም ነው ያነሱት። የወባ ትንኝ መራቢያ ቦታዎችን ለይቶ ማኅበረሰቡን በማሳተፍ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ በትኩረት አለመሥራት፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የመኝታ አጎበር በወቅቱ አለመተካቱ እና ማኅበረሰቡም የተሰጠውን የመኝታ አጎበር በአግባቡ አለመጠቀም ለወባ በሽታ ጭማሬው እንደ ዋና ምክንያት ተቀምጠዋል።

በኬሚካል እጥረት ምክንያት የፀረ ወባ ትንኝ ኬሚካል ርጭት የሚካሄድባቸው ቀበሌዎች ቁጥር መቀነስ፣ ወደ ወባማ አካባቢዎች የሚደረግ የሰዎች እንቅስቃሴ እና ከፍተኛ የኾነ የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ በክልሉ መኖር ለሥርጭቱ ሌላው ምክንያት ኾኖ ተቀምጧል። ሥርጭቱን ለመከላከል ባለፉት ወራት ከፍተኛ የወባ ጫና ባለባቸው 27 ወረዳዎች በሚገኙ 233 ቀበሌዎች የቤት ውስጥ የጸረ ወባ ትንኝ ኬሚካል ርጭትም ተካሂዷል።

ከጥቅምት 15/2017 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ዘወትር አርብ “የአርብ ጠንካራ እጆች የወባ በሽታን ይገታሉ” በሚል መሪ መልዕክት ለተከታታይ 11 ሳምንታት ክልላዊ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ ዘመቻ እየተሠራ ይገኛል። የወባ በሽታን ለመቆጣጠር በማኅበረሰቡ ተሳትፎ እና ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሠራ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል።

ጤና ተቋማትም የወባ መከላከልን መደበኛ ሥራ አድርገው በትኩረት እንዲሠሩም አሳስበዋል። ታኅሣሥ 25/2017 ዓ.ም በክልሉ ሁሉም ወባማ ቀበሌዎች የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከጠዋቱ 1 ሰዓት እስከ 2 ሰዓት የወባ ትንኝ መራቢያ ቦታዎችን የማፋሰስ፣ የማዳፈን እና የማጽዳት ሥራ እንዲሠሩም ጠይቀዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleመጭዎቹ ሃይማኖታዊ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ኅብረተሰቡ ሚናውን እንዲዎጣ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ።
Next articleየገበያ ማዕከላትን በማስፋት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት በትኩረት እየተሠራ ነው።