መጭዎቹ ሃይማኖታዊ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ኅብረተሰቡ ሚናውን እንዲዎጣ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ።

34

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ረዳት ኮሚሽነር መሠረት ደባልቄ እንዳሉት የሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲጠናቀቁ የሚሊሻ እና የፖሊስ አካላት ዝግጅታቸውን አጠናቅቀዋል። ኅብረተሰቡም ከጸጥታ ኀይሉ ጋር በቅንጅት መሥራት ይኖርበታል ነው ያሉት።

ክልሉ ከገጠመው የጸጥታ ችግር አኳያ በዚህ ዓመት በዓላቱን በሰላም ለማክበር ልዩ ዝግጅት ስለመደረጉም አስገንዝበዋል። በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ማኅበረሰቡ ከየትኛውም አካባቢ መጥቶ በዓላቱን እንዲያከብር ሥራዎች እየተሠሩ ነው ያሉት ረዳት ኮሚሽነሯ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከወጣቶች እና ከኅብረተሰቡ ጋር ውይይት ተደርጓል ነው ያሉት። መግባባት ላይም ተደርሷል ብለዋል።

ሰላም ወዳዱ የክልሉ ሕዝብ አሁን ብቻ ሳይኾን ባሳለፍናቸው ጊዜያቶችም በክልሉ የተከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ አደረጃጀቶችን ፈጥሮ ቀን እና ሌሊት በመሥራት የሰላም ዘብነቱን ማረጋገጡን ኀላፊዋ ተናግረዋል። በየትኛውም የክልሉ አካባቢዎች የንግድ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር እና ግብይት ይኖራል ያሉት ረዳት ኮሚሽነር መሠረት ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ከሕገ ወጥ ድርጊታቸው እንዲታቀቡም አሳስበዋል።

በዓላቱን መሠረት ያደረጉ የዋጋ ጭማሪ እና ሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲኖር በማድረግ ማኅበረሰቡን መመዝበር ሊቆም ይገባዋልም ብለዋል። የንግዱ ማኅበረሰብም በበዓላት ወቅት እንግዶችን ለማስተናገድ ከነበረው ዋጋ ሳይጨምር በቀናነት ማስተናገድ ይኖርበታም ነው ያሉት ረዳት ኮሚሽነሯ።

በበዓል ሰሞን በከፍተኛ ኹኔታ የእንስሳት ግብይት ይከናወናል ያሉት ረዳት ኮሚሽነሯ በተለይ አርሶ አደሩ ግብይት እና የገንዘብ ዝውውር ሲያደርግ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበትም አሳስበዋል። ሐሰተኛ የገንዘብ ዝውውር በበዓላት ወቅት በብዛት ሊኖር ስለሚችልም ተገበያዮች ግብይታቸውን በባንክ እንዲያከናውኑም ፖሊስ መክሯል።

በበዓላት ወቅት ከፍተኛ ጉዞ ይኖራል ያሉት ረዳት ኮሚሽነር መሠረት በከፍተኛ ኹኔታ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ይኖራልም ብለዋል። በዚህ ወቅት አደጋ እንዳይከሰት የትራፊክ ፖሊሶች ከሌሎች ቀናት በበለጠ 24 ሰዓታት ይሠራሉ ነው ያሉት። ሌሎች የጸጥትታ ኀይላትም ጸጥታን ከማስፈን ጎን ለጎን ጤነኛ የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲኖር ሥራቸውን ይከውናሉ ብለዋል።

ማኅበረሰቡ ያለአግባብ ክፍያ እንዳይከፍል፣ ትርፍ እንዳያሳፍር፣ ሕገ ወጥ ድርጊት ሲገጥመው እና ሲመለከት በአካል እና በስልክ በመጠቆም መተባበር ይገበዋል ነው ያሉት። በበዓላት ወቅት የወንጀል ድርጊት ሲፈጸም ፈጣን ፍትሕ እንዲሰጥ በተለይ በላሊ በላ እና ጎንደር የምርመራ ቡድን ተዋቅሯል ብለዋል።
በዚህ መልኩ ወንጀልን ለመከላከል ዝግጅቱ ተጠናቅቆ ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል ረዳት ኮሚሽነሯ።

ማኅበረሰቡ በተለይ ወጣቶች ከመቼውም የበዓላት ወቅት በተለዬ ኹኔታ ለክልሉ ሰላም ዘብ እንዲቆሙ ነው ረዳት ኮሚሽነር መሠረት ደባልቄ ጥሪ ያቀረቡት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአካባቢያችን ሰላም መኾኑ ትምህርታችን ላይ እንድናተኩር አግዞናል” ተማሪዎች
Next articleማኅበረሰቡ የወባ ትንኝ መራቢያ ቦታዎችን የማፋሰስ፣ የማዳፈን እና የማጽዳት ሥራ እንዲሠራ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) አሳሰቡ።