
ሁመራ፡ ታኅሣሥ 24/04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አካባቢያቸው ሰላም በመኾኑ ትምህርታቸውን ተረጋግተው እንዲማሩ እንዳስቻላቸው በሁመራ ከተማ አሥተዳደር የሰቲት ሁመራ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ለአሚኮ ተናገረዋል። የ10ኛ ክፍል ተማሪዋ ለምለም ወንድሙ የአካባቢው ሕዝብ እና ተማሪዎች ከዚህ በፊት የገጠመው የሰላም እጦት እንደጎዳቸው ገልጻለች።
አሁን የተፈጠረው ሰላም ትምህርታቸውን በሚገባ ተምረው የሚፈልጉትን ውጤት ለማሳካትም እያገዛቸው እንደኾነ ነው የተናገረችው። የ12ኛ ክፍል ተማሪው ተመስገን አዘዘ እንደተናገረው አካባቢያቸው ሰላም በመኾኑ ሕልምና ዓላማቸውን ለማሳካት እያገዛቸው ነው። የሰላሙ ኹኔታ ትምህርታቸው ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርጉ እንዳገዛቸውም ነው የጠቆመው።
“አሁን ያለው ሰላም በትምህርታችን ውጤታማ እንድንኾን አድርጎናል” ያለው ተማሪው አሁን ላይ የሰላም እጦት ሊያስከትል ከሚችለው የሥነ ልቦና ጫና ነፃ ኾነው እየተማሩ መኾኑንም አስረድቷል። የሰላምን አስፈላጊነት ለማስገንዘብ የተለያዩ ተግባራትን እየከወኑ እንደኾነ የተናገሩት በትምህርት ቤቱ የሥነ ልቦና እና የምክር አገልግሎት ባለሙያ ያለው ዘለቀ ናቸው።
ባለሙያው የተፈጠረው ሰላም ተማሪዎች በተረጋጋ መንፈስ እንዲማሩ ማስቻሉንም አስገንዝበዋል። ለሰላም ትኩረት በመስጠት የሰላም ክበብ ማቋቋማቸውንም ጠቁመዋል። ከመደበኛው የጸጥታ መዋቅር በተጨማሪ ኅብረተሰቡን በማደራጀት ለመማር ማስተምሩ ምቹ ኹኔታ እንደተፈጠረም ተገልጿል።
የሁመራ ከተማ አሥተዳደር የሰላም እና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ ኢንስፔክተር ክንፈ ንጉሴ የባጃጅ አሽከርካሪዎችን በማደራጀት ሰላሙን እንዲጠብቁ እና የመማር መስተማሩን ተግባር እንዲደጎፉ መደረጉን ገልጸዋል። የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ትምህርት መምሪያ ተወካይ ኀላፊ አስረሳ ወንድይፍራ በሰላም ዙሪያ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት መማር ማስተማሩ እንዳይደናቀፍ እየሠሩ መኾኑን ተናግረዋል።
በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ተካሂዶ በነበረው ጦርነት በርካታ ትምህርት ቤቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው የሚገልጹት ተወካይ ኀላፊው በሀገር እና ከሀገር ውጭ የሚኖሩ ወገኖች የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አስተላልፈዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!