
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን መጭዎቹን ሃይማኖታዊ በዓላት በሰላም ተከብረው እንዲጠናቀቁ ኅብረተሰቡ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በመኾን ሕገ ወጥ ድርጊቶችን አስቀድሞ እንዲከላከል አሳስቧል።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ረዳት ኮሚሽነር መሠረት ደባልቄ በክልሉ የሐሰተኛ የብር ኖት ዝውውር የወንጀል ተግባር በተደጋጋሚ ተከስቷል ብለዋል። የጸጥታ ኃይሉ ኅብረተሰቡን ግንዛቤ ከማስጨበጥ ባለፈ የወንጀሉን ፈጻሚዎች ተከታትሎ በቁጥጥር ሥር እያዋለ እንደኾነ ገልጸዋል።
ባለፈው ሩብ ዓመት” ከ200 ሺህ ብር በላይ የሐሰተኛ የብር ኖት ሲዘዋወር ተይዟልም “ነው ያሉት ረዳት ኮሚሽነሯ።
የሐሰተኛ የብር ኖት በክልሉ በሁሉም ቦታዎች እንደሚዘዋር የጠቆሙት ኮሚሽነሯ በተለይ በባሕር ዳር ከተማ፣ አዊ እና በዋግ ኽምራ በከፍተኛ ኹኔታ የሐሰተኛ የብር ኖት ዝውውር ተከስቷል፤ በቁጥጥር ሥርም ውሏል ብለዋል። አርሶ አደሩ እና የንግዱ ማኅበረሰብ በስፋት ግብይት በሚያደርግበት የበዓላት ወቅት ወንጀል ፈጻሚዎች የሐሰት የብር ኖት አሳትመው በመዘዋወር ለኪሳራ ይዳርጋሉ፤ ሰላማዊውን ገበያም ያውካሉ ብለዋል።
ይህም ከግለሰብ ባለፈ የሀገርን ምጣኔ ሐብት እና ገጽታ ይጎዳል ነው ያሉት። የወንጀል ፈጻሚዎች በተለይ በበዓል ሰሞን የእርድ እንስሳት ወደ ገበያ መውጣታቸውን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ሐሰተኛ የብር ኖት በሥፋት ሊያዘዋውሩ ስለሚችል ኅብረተሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግም ረዳት ኮሚሽነር መሠረት አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!