
ደሴ: ታኅሣሥ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ወሎ ዞን ጤና መምሪያ “እንደ አቅሜ አዋጣለሁ፤ እንደ ሕመሜ እታከማለሁ” በሚል መሪ መልዕክት ዞናዊ የ2017 ዓ.ም የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል፡፡ በመድረኩ በባለፈው በጀት ዓመት እንደ ሀገርም ኾነ እንደ ክልል የደቡብ ወሎ ዞን የላቀ ውጤት ማስመዝገቡ የተጠቀሰ ሲኾን፤ የአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ እና የለገሂዳ ወረዳ ደግሞ በዞኑ ከሚገኙ ወረዳዎች የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገብ መቻላቸው ተገልጿል።
የአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ ሲስተር መሬማ ሙሐመድ ማኅበረሰቡ ስለጤና መድኅን በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው በመሠራቱ ከዕቅዳቸው የላቀ ውጤት ማስመዝገብ እንደቻሉ ይናገራሉ። በዚህ ዓመትም ሙሉ ማኅበረሰቡ የጤና መድኅን አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሠሩም ገልጸዋል።
የለገሂዳ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሐብታሙ ታከለ ባለፈው በጀት ዓመት ከ15 ሺህ በላይ የጤና መድኅን አባል ማፍራታቸውን ጠቅሰው ይህም ከዕቅዳቸው በላይ መኾኑን ተናግረዋል። ጤና መድኅን ዓላማው ከድንገተኛ የሕክምና ወጭ ዜጎችን መታደግ መኾኑን ገልጸው ዘንድሮም የነበሩትን ጥንካሬዎች ለማስቀጠል እንደሚሠሩ ነው ያስረዱት።
ባለፉት ዓመታት ዞኑ ከፍተኛ አፈጻጸም ማምጣት መቻሉን የተናገሩት የደቡብ ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ኀላፊ ጌታቸው በለጠ ባለፈው ዓመት ከ77 በመቶ በላይ የሚኾነውን የኅብረተሰብ ክፍል በማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
ከዛም ባለፈ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ሃብት መሠብሠብ መቻሉን እና ከ2 ሚሊዮን በላይ የኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ እንደኾነ አንስተዋል፡፡ ከዚህም ውስጥ 51 በመቶ የሚኾኑት ሴቶች መኾናቸውንም አቶ ጌታቸው ጠቁመዋል፡፡
በዚህ ዓመትም ከአሁን በፊት በቤተሰብ ብዛት ሲዋጣ የነበረው ቀርቶ እንደ አቅማቸው ሊያዋጡ እና እንደ ሕመማቸው ሊታከሙ የሚችሉበት ወጥነት ያለው አሠራር እንደ ሀገር መዘርጋቱንም ገልጸዋል፡፡
በተያዘው ዓመት ከ579 ሺህ በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የጤና መድኅን ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱንም ጠቁመዋል። ይህንም ለማሳካት ከ630 ሚሊዮን ብር በላይ ሃብት ለመሠብሠብ እንደሚሠራም አንስተዋል፡፡
ዘጋቢ፦ መስዑድ ጀማል
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!