“የሃይማኖት ተቋማት ትብብርና አብሮነት ለሰላም ግንባታ ሂደት ትልቅ ሚና አለው” የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ

28

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በቅርብ ወደኀላፊነት የመጡት የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ ከኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ጋር ትውውቅ አድርገዋል። ሚኒስትሩ “የሃይማኖት ተቋማት ትብብርና አብሮነት ለሰላም ግንባታ ሂደት ትልቅ ሚና አለው” ሲሉ በትውውቅ ፕሮግራሙ ላይ ገልጸዋል። በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ጉዳይ ሰላማዊና የተረጋጋ ማኅበረሰብ እንዲኖር የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ አስተዋጽኦ ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል በቀጣይ በሰላም ግንባታ ሥራዎች ላይ እያከናወነ ያለውን ተግባር አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አሳስበዋል። የሰላም ሚኒስቴርም በትብብርና በቅንጅት ከካውንስሉ ጋር ለመሥራት ያለውን ዝግጁነትም አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ፕሬዚዳንት ጣሰው ገብሬ (ዶ.ር) ከመገፋፋት ይልቅ በመተባበር እና በመደጋገፍ ለሀገራችን ሰላም መረጋገጥ ሃይማኖቶች ትልቅ አቅም ሊሆኑ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆን ሲሠራ የቆያቸውን የሰላም ግንባታ ሥራዎች አጠናክሮ በማስቀጠል በሰላም ጉዳይ የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ ስለመኾኑም ጠቁመዋል።

የሰላም ሚኒስቴር አመራሮች፣ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አመራሮች እና የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል አባላት በትውውቅ ፕሮግራሙ ተገኝተዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አባቶቻችን ያስቀመጡልንን ሥርዓት እንጠብቃለን” አባ ሕርያቆስ ጸጋዬ
Next articleከ570 ሺህ በላይ የቤተሰብ ኀላፊዎችን የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን የደቡብ ወሎ ዞን አስታወቀ።