“አባቶቻችን ያስቀመጡልንን ሥርዓት እንጠብቃለን” አባ ሕርያቆስ ጸጋዬ

43

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ላሊበላ እንግዶቿን እግር እያጠበች መቀበሏን ቀጥላለች። የደብረ ሮሐ ቅዱስ ላሊበላ መነኮሳት፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና የከተማዋ ነዋሪዎች እንግዶችን እግር እያጠቡ በመቀበል ተጠምደዋል። ሁሉም በረከት ለማግኘት ሲፋጠኑ ይውላሉ። የእንግዶችን ጓዝ እየተቀበሉ በጥላ ያሳርፋሉ። ከእግራቸው ሥር ኾነው እግር ያጥባሉ። አክብሮትም ይሰጣሉ። በረከት አይለፈኝ በሚል ያለው እሽቅድምድም ቀጥሏል።

እንግዶችን ዝቅ ብለው እግር በማጠብ የሚቀበሉት የደብረ ሮሐ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም አሥተዳዳሪ አባ ሕርያቆስ ጸጋዬ አባቶቻችን የልደትን በዓል በላሊበላ ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን እግር እያጠቡ ሲቀበሉ ኖረዋል ነው ያሉት። እኛም አባቶቻችን ያስቀመጡልንን ሥርዓት እና ያስረከቡንን ትውፊት ለመጠበቅ ኀላፊነት እና አደራ አለብን ብለዋል። አባቶቻችን ያስቀመጡልንን ሥርዓት እንጠብቃለን ነው ያሉት።

እግር በማጠብ ትህትናን ያስተማረን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ብለዋል አባ ሕርያቆስ። ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር የነበረውን የወንጌል አገልግሎት ፈጽሞ የመጨረሻው ራት ጊዜ ያደረገው በትህትና ዝቅ ብሎ የሐዋርያትን እግር ማጠብ ነበር ነው ያሉት። እግር ማጠብ የትህትና ምልክት ነው ያሉት አባ ሕርያቆስ መንፈሳዊ ሥራዎች ከሚገለጡባቸው ተግባራት መካከል አንደኛው መኾኑንም ገልጸዋል። ጌታ ተንበርክኮ የሐዋርያትን እግር አጥቧል፣ ካጠባቸውም በኋላ እናንተም ለባልንጀራችሁ አድርጉት ብሎ ትዕዛዝ ሰጠ ብለዋል። ቤተክርስቲያንም ቃሉን እና ትዕዛዙን መሠረት አድርጋ እግር እያጠበች ተገቢውን የእንግዳ አቀባበል ሥርዓት ትፈጽማለች ነው ያሉት። እኛም ቤተክርስቲያን ባስተማረችን፣ ጌታችን ባዘዘን እና አባቶቻችን ባቆዩን ሥርዓት መሠረት እግር እናጥባለን ብለዋል።

ከፍቅር ሁሉ የሚቀድመው ባልንጀራን መውደድ ነው ያሉት አባ ሕርያቆስ ከአባቶቻችን በተቀበልነው ሥርዓት እና ትውፊት መሠረት እንግዶቻችንን እግራቸውን እያጠብን ነው፣ ይሄንም ሥርዓት ለልጆቻችን እናስተላልፋለን ነው ያሉት። የሚገቡ እንግዶችን እግር እያጠቡ እንኳን ደህና መጣችሁ የሚሉት የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ወንድምነው ወዳጅ የቅዱስ ላሊበላ ሕዝብ እንደተለመደው ባማረ የእንግዳ አቀባበል ባሕል እንግዶችን እየተቀበለ ነው ብለዋል። በረከት ባለው እና ተስፋ በሚሰጥ ተግባር እየተሳተፉ መኾናቸውንም ገልጸዋል።

ስንጓጓለት የነበረው በዓል ደርሶ እንግዶችን እግር እያጠብን እየተቀበልን ነው ብለዋል። ዝቅ ብለን እግር እያጠብን እንግዶችን ለመቀበል ስለደረስን እና ስለበቃን ደስተኞች ነን ነው ያሉት። የእንግዳ አቀባበል እና ዝቅ ብሎ ማገልገል የቆዬ ባሕላቸው እና ትውፊታቸው መኾኑንም ገልጸዋል።

የእንግዳ አቀባበል ትውፊታችን እና በረከት የሚገኝበት ሥርዓታችን እንዲቀጥል ሰላምን ማስጠበቅ ወሳኝ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ልደት ደግሞ የሰላም፣ የፍቅር እና የበረከት በዓል ነው ብለዋል። የተወደደውን ባሕል እና ትውፊት ይዞ ለመዝለቅ ሰላም ላይ መሥራት እና የቆየውን ሥርዓት መጠበቅ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

የሰሜን ወሎ ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ገነት ሙሉጌታ ለልደት በዓል ወደ ላሊበላ የሚገቡ እንግዶችን ባማረ የእንግዳ አቀባበል መቀበል የሚያስደስት መኾኑን ተናግረዋል። እግር እያጠቡ እንግዶችን መቀበል መልካም እና የቆየ እሴት መኾኑን ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከ9 ሺህ በላይ በሚኾኑ ተፋሰሶች ላይ የተፈጥሮ ሃብት ሥራ ይሠራል” የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ
Next article“የሃይማኖት ተቋማት ትብብርና አብሮነት ለሰላም ግንባታ ሂደት ትልቅ ሚና አለው” የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ