“ከ9 ሺህ በላይ በሚኾኑ ተፋሰሶች ላይ የተፈጥሮ ሃብት ሥራ ይሠራል” የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ

82

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከጥር/2017 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ተግባር እንደሚገባ የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ደረጀ ማንደፍሮ ገልጸዋል። ምክትል ኀላፊው እንዳሉት በ2017 በጀት ዓመት በአማራ ክልል በ9 ሺህ 87 ተፋሰሶች 366 ሺህ 649 ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ የሥነ አካላዊ፣ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራዎች ይከናወናሉ።

እስከ አሁን ከ3 ሚሊዮን 980 ሺህ በላይ የቅየሳ መሣሪያዎች ልየታ ሥራ ተሠርቷል። በልማት ሥራው ላይ ከ4 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ የሰው ሃይል ይሳተፋል። በ384 ሺህ 504 ሄክታር መሬት ላይ በሥነ ሕይወታዊ መንገድ የአፈር ለምነትን ማሻሻል ሥራ የሚሠራ ይኾናል። ከ12 ሺህ 800 በላይ ሄክታር ውኃማ እና የየብስ መሬትን ከወራሪ እና አደገኛ አረሞች ነፃ ለማድረግ ታቅዷል።

ሌላው ትኩረት የተሠጠው ተግባር የአረንጓዴ አሻራ ልማት ሥራ ነው። የክልሉን የደን ሽፋን አሁን ካለበት 16 ነጥብ 3 በመቶ ወደ 17 ነጥብ 3 በመቶ ለማድረስ እየተሠራ ነው። ለዚህም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን በላይ የተለያዩ የእፅዋት ችግኞችን የማዘጋጀት ሥራ እየተሠራ ነው።

በክልሉ ለሚከናወነው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ውጤታማነት ለማረጋገጥ ዞኖች ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ መደረጉንም ምክትል ኀላፊው ገልጸዋል። የተፈጥሮ ሃብት ሥራ ከሚሠራባቸው ዞኖች ውስጥ ደግሞ ሰሜን ጎጃም ዞን አንዱ ነው። የዞኑ ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ መልካሙ አለኸኝ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት በዞኑ ከጥር/2017 ዓ.ም ጀምሮ የተፈጥሮ ሃብት ሥራን ለማስጀመር የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ ይገኛል።

በዞኑ 470 ተፋሰሶች ተለይተዋል። ከ12 ሺህ በላይ ኪሎ ሜትር የደረጃ ማሳደግ፣ 551 ኪሎ ሜትር የውኃ ማስወገጃ፣ ከ1 ሚሊዮን 782 ሺህ በላይ የሚኾኑ የርጥበት እቀባ ትሬንች፣ ማይክሮ ቤዝን የመሳሰሉ የስትራክቸር አይነቶች መለየታቸውን ገልጸዋል።

በተፈጥሮ ሃብት ሥራው ከ242 ሺህ በላይ የሰው ኀይል ይሳተፋል ተብሎ ይጠበቃል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በነዳጅ ጉዳይ ነጋዴዎች ባለ አደራ እንጂ ባለቤቶች አይደላችሁም” ኢብራሂም መሐመድ (ዶ.ር)
Next article“አባቶቻችን ያስቀመጡልንን ሥርዓት እንጠብቃለን” አባ ሕርያቆስ ጸጋዬ