“በነዳጅ ጉዳይ ነጋዴዎች ባለ አደራ እንጂ ባለቤቶች አይደላችሁም” ኢብራሂም መሐመድ (ዶ.ር)

46

ደሴ: ታኅሣሥ 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ወሎ ዞን ንግድ እና ገበያ ልማት መምርያ በነዳጅ ስርጭት፣ ርክክብ እና ሽያጭ መመሪያ እና የአፈጻጸም ጉድለቶች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በደሴ ከተማ ውይይት አካሂዷል። ውይይቱን የመሩት የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኅላፊ ኢብራሂም መሐመድ (ዶ.ር) ሀገራችን ለነዳጅ በዓመት እስከ 4 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንደምታደርግ ገልጸዋል።

ከፍተኛ ወጪ የወጣበት ሐብት በአግባቡ ሕዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ “በነዳጅ ጉዳይ ነጋዴዎች ባለ አደራ እንጂ ባለቤቶች አይደላችሁም” ሲሉ ተናግረዋል። አሠራር እና መመሪያን ተገንዝባችሁ፤ መብት እና ግዴታችሁን አውቃችሁ፤ ሕዝባችሁን ማገልገል አለባችሁም ብለዋል። ቁጥጥር ለሚያደርገው አካልም አጋዥ መኾን እንደሚገባም አሳስበዋል።

ነዳጅ መንግሥት ከፍተኛ ወጪ አውጥቶ ሕዝቡን በድጎማ ሥርዓት ተጠቃሚ የሚያደርግበት ኹኔታ እየተተገበረ ቢኾንም መመሪያውን እና አሠራሩን በተገቢው ኹኔታ ባለማወቅ ብዙ ችግሮች እያጋጠሙን ነው ብለዋል። የዚህ ውይይት ዓላማም በመመሪያው ላይ ግልጸኝነትን በመፍጠር እየተስተዋሉ ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት እና የጋራ መግባባትን ለመፍጠር ያለመ ነው ያሉት ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ተስፍ መንግሥቴ ናቸው።

የነዳጅ ግብይቱን ጤናማ በማድረግ የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሠራ መኾኑንም መምሪያ ኅላፊው ተናግረዋል። መምሪያ ኀላፊው ችግሮች ብለው ያነሷቸው ማደያዎች ላይ ነዳጅን እንደማንኛውም ሸቀጥ የመሸጥ ኹኔታ እና አትቆጣጠሩን የሚል ችግር ለባለሙያዎች ማሳየት፤ መጠባበቂያ ነጃጅ ወሩ መጨረሻ ላይ እንዲያስቀምጡ መመሪያው ቢያዝም አለመፈጸም፤ ለሕገ ወጥ ነጋዴዎች አሳልፎ መሸጥ እና በአግባቡ ርክክብ አለመፈጸም ዋና ዋናዎቹ ናቸው ብለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ ነጋዴዎች አሉ ያሏቸውን ችግሮች አንስተዋል። ዋና ችግር ተደርጎ የተጠቀሰው የነዳጅ አቅርቦት ላይ የመቆራረጥ ችግር በተለይም የቤንዚን ችግር አብይ ጉዳይ መኾኑን ገልጸዋል ። በተጨማሪም መኪና ነዳጅ ለማምጣት ሄዶ ጂቡቲ ላይ ለወራት መቆየቱ ችግር እንደፈጠረባቸው ጠቅሰዋል።

በውይይቱ የዞን፣ የወረዳ እና የከተማ መሥተዳድር ንግድ እና ገበያ ልማት ኅላፊዎች እና ባለሙያዎች፣ የፍትሕ አካላት እና የነጃጅ ማደያ ባለቤቶች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ: መሐመድ በቀለ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ዝግጅት አጠናቅቀን እንግዶችን እየተቀበልን ነው” የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር
Next article“ከ9 ሺህ በላይ በሚኾኑ ተፋሰሶች ላይ የተፈጥሮ ሃብት ሥራ ይሠራል” የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ