
ወልድያ: ታኅሣሥ 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የልደት በዓል በቅዱስ ላሊበላ በታላቅ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ይከበራል። በክብረ በዓሉ በርካታ አማኞች እና እንግዶች ይገኛሉ። በታላቁ ሥፍራ በዓሉን ለማክበር ቀደም ብለው የተነሱ እንግዶች ላሊበላ ደርሰዋል። አስቀድመው የደረሱ እንግዶች በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት አጸድ ሥር በጸሎት እየበረቱ፣ ረቂቁን ሥራ እየተመለከቱ ነው።
ላሊበላ ያልደረሱት ደግሞ በጉጉት እየተጠበቁ ነው። የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር እና የከተማዋ ነዋሪዎችም አስቀድመው ዝግጅታቸውን አጠናቅቀው እንግዶችን እየተቀበሉ ነው። የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዲያቆን አዲሴ ደምሴ የልደት በዓልን ለማክበር ልዩ ልዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን አከናውነን ጨርሰናል ብለዋል። አሁን ላይ እንግዶችን እየተቀበሉ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
እንግዶች የሚያርፉባቸው ሆቴሎች እና ሌሎች አማራጮችን ማዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል። እንግዶች በሆቴሎች እና በቤተክርስቲያን አጸድ ሥር እንደሚያርፉም ገልጸዋል። የሚመጡ እንግዶች የማረፊያ ችግር አይገጥማቸውም ነው ያሉት። የከተማዋ ወጣቶች እየገቡ ያሉ እንግዶችን እግር እያጠቡ እየተቀበሏቸው ነው። በከተማዋ ያሉ እድሮች እንጀራ እያዋጡ ለእንግዶች እያቀረቡ መኾናቸውን ገልጸዋል። የበዓሉ ቀንም እንግዶችን ጾም እያስፈቱ እንደሚሸኟቸው ነው የተናገሩት።
የቅዱስ ላሊበላ አብያተክርስቲያናት በኢትዮጵያ ግንባር ቀደም የቱሪዝም መዳረሻ መኾናቸውን የተናገሩት ኀላፊው ከተማዋ የዓለምን ቅርስ የያዘች የዓለም ከተማ መኾኗንም ገልጸዋል። የከተማዋ ነዋሪዎች የገቢ ምንጫቸው ቱሪዝም መኾኑንም አንስተዋል። የልደት በዓል ከፍተኛ የቱሪዝም መነቃቃት እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች የዓመት ልብሳቸውን እና ጉርሳቸውን የሚያገኙት ከልደት በዓል ላይ መኾኑን ነው የተናገሩት። የልደት በዓል ከሃይማኖታዊ በዓልነቱ ባሻገር ለላሊበላ ከተማ ልዩ ትርጉም አለው ነው ያሉት። በዓሉ ሙሉ ለሙሉ ተቀዛቅዞ የነበረውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለመመለስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ተናግረዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች የልደትን በዓል በጉጉት እንደሚጠብቁትም ገልጸዋል። በችግር ውስጥ የቆዬውን ቱሪዝም ለመመለስ በዓሉን በድምቀት ማክበር ትልቅ ፋይዳ አለው ነው ያሉት። ከበዓሉ በኋላም የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኝዎች ላሊበላን እንዲጎበኙ እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል። ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላትን በድምቀት ማክበር ለቱሪዝም ዕድገት ፋይዳው ከፍተኛ መኾኑንም አመላክተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!