
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 5 ሚሊዮን ኢትዮ ኮደርስ በተባበሩት አረብ ኤምሬት ተባባሪነት ለኢትዮጵያውያን የሚሰጥ ነጻ የቴክኖሎጅ ሥልጠና ነው። ሥልጠናውን ማንኛውም ሰው መውሰድ የሚችል ሲኾን በመጨረሻም የምሥክር ወረቀት ያስገኛል። ሥልጠናው ለሦስት ተከታታይ ዓመታት እንደሚሰጥም ይታወቃል። ሥልጠናው ከተጀመረ ስድስት ወራት ተቆጥረዋል።
የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ እርዚቅ ኢሳ በአማራ ክልል በሦስት ዓመታት ውስጥ 760 ሺህ ወጣቶችን የሥልጠናው ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ ነው ብለዋል። ከዚህ ውስጥ 171 ሺህ የሚኾኑ ወጣቶች ሥልጠናውን በዚህ ዓመት እንዲወስዱ ታቅዷል። በዚህ መሰረት ለወጣቶች ስለሥልጠናው አስፈላጊውን ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ሲከናወን ቆይቷል ነው ያሉት።
ከ34 ሺህ በላይ ወጣቶች በዚህ ሰዓት ሥልጠናውን እየተከታተሉ ስለመኾኑም ጠቁመዋል። 22 ሺህ 321 ወጣቶች ደግሞ ሥልጠናውን አጠናቅቀው ወረቀት አግኝተዋል። ሥልጠናው የቴክኖሎጂ ክፍተቶችን የሚሞላ እና ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉትም ተጠቅሷል። ይሁን እንጅ ይህንን ሥልጠና ለመውሰድ በርካታ ተግዳሮቶች እንዳጋጠሙም በውይይቱ ተጠቁሟል።
የኢንተርኔት ችግር፣ የአመራር ትኩረት ማነስ፣ አጋር አካላትን በማሳተፍ በኩል ያለ ውስንነት እና የመሳሰሉት እንደ ተግዳሮት ተነስተዋል። ችግሮቹ ተፈትተው ሥልጠናው እንዲሰጥ ለማድረግ እስከ ርእሠ መሥተዳድሩ የደረሰ ውይይት ተደርጓል፤ ኮሚቴው ተጠናክሮ ችግሮችን እንዲፈታም ተሠርቷል።
ሥልጠናውን እስካሁን ድረስ ያለኢንተርኔት መውሰድ አይቻልም ነበር። ኢትዮ ቴሌኮም ባደረገው ትብብር መሰረት ከዚህ በኃላ የኢትዮ ኮደርስ ሥልጠናን ከክፍያ ነጻ በኾነ የኢንተርኔት አገልግሎት መሠልጠን እንደሚቻልም ተገልጿል። ሥልጠናው የራስ ክህሎት ከማበልጸግም በላይ ለክልሉ እና ለሀገር ተወዳዳሪ ዜጋን የሚፈጥር በመኾኑ ወጣቶች መሠልጠን እንዳለባቸው አቶ እርዚቅ አሳስበዋል።
በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የግል ዘርፍ ኢንዱስትሪ ቴክኖሎጂ ድጋፍና ክትትል ዴስክ ኀላፊ መስፍን ሽፈራው በአማራ ክልል ያለው የስድስት ወር የኢትዮ ኮደርስ የሥልጠና ሂደት ሥራውን በሚያቀላጥፍ አደረጃጀት እየተመራ ስለመኾኑ ገልጸዋል። በተለይም የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች ጠንካራ እንደነበሩ ጠቁመዋል። በወጣት ማዕከላት፣ በኮሌጆች፣ በዩኒቨርሲቲዎች፣ እና በሌሎችም ተቋማት ድረስ በመዝለቅ ወጣቶች ሥልጠናውን እንዲወስዱ ግንዛቤ መፈጠሩን ገምግመናል ነው ያሉት።
በሥልጠናው ላይ ያጋጠሙ ችግሮች ተቀርፈው ሥልጠናው በተሳካ ኹኔታ ተደራሽ እንዲኾን ለማስቻል የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል። በተለይም ኢትዮቴሌኮም ለሥልጠናው የፈቀደው ነጻ የኢንተርኔት አገልግሎት ሥልጠናውን ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ እገዛ ይኖረዋል ብለዋል። ወጣቶች ይህንን እድል በመጠቀም ዕውቀት እና ክህሎታቸውን መገንባት እና በውድድር ዓለም ውስጥ ብቁ ኾነው መገኘት እንዳለባቸውም ኀላፊው አስገንዝበዋል።
የአማራ ክልል ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር የቻለ ይግዛው የኢትዮ ኮደርስ ሥልጠና ለክልሉ ወጣቶች ተደራሽ እንዲኾን በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል። ኮሚሽኑ የሥልጠናውን ሥራ በዋናነት እያስተባበረ ሲኾን በኮሚሽኑ ግቢ ውስጥ የሥልጠና ማዕከላትን በማመቻቸት ወጣቶች ሥልጠናውን እየወሰዱ ነው።
ሥልጠናው የቴክኖሎጂ ክፍተቶችን የሚሞላ እና የወጣቶችን ክህሎት የሚያሳድግ በመኾኑ በትኩረት መውሰድ ያስፈልጋል ነው ያሉት። በዲጂታል ዓለም ውስጥ ተወዳዳሪ ለመኾን የሚያስችል በቴክኖሎጂ የዳበረ ትውልድ መገንባት ግድ ይላል፤ 5 ሚሊየን ኢትዮ ኮደርስ ለዚህ ትልቅ አጋዥ በመኾኑ
ልንጠቀምበት እንደሚገባም ተጠቁሟል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!