
ወልድያ: ታኅሣሥ 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በደብረ ሮሐ ቅዱስ ላሊበላ በታላቅ ሥርዓት ይከበራል። ታላቁን በዓል በተቀደሰው ሥፍራ የሚያከብሩ አማኞች እና እንግዶች ደግሞ ከበዓሉ ቀደም ብለው ወደ ላሊበላ እየገቡ ነው። የደብረ ሮሐ ቅዱስ ላሊበላ ገዳምም ቀድመው የመጠትን እየተቀበለች ነው። የሚመጡትንም ለመቀበል ዝግጅቷን ጨርሳ እየጠበቀች ነው።
የደብረ ሮሐ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም አሥተዳዳሪ አባ ሕርያቆስ ጸጋዬ የልደት በዓልን በቅዱስ ላሊበላ ማክበር ክብሩ ታላቅ ነው ብለዋል። የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ከ800 በላይ ለሚኾኑ ዓመታት በቅዱስ ላሊበላ በድምቀት ሲከበር መኖሩን ገልጸዋል። ቅዱስ ላሊበላ የረቀቁትን አብያተክርስቲያናት ካነጸ በኋላ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በዚሁ ሥፍራ እንዲከበር ማድረጉን ገልጸዋል። ይሄም የኾነው በራሱ ፈቃድ ሳይኾን በተማጽኖ ከአምላኩ ባገኘው ፈቃድ ነው ብለዋል።
በቅዱስ ላሊበላ አብያተክርስቲያናት የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት የሚያከብሩ ሁሉ በሰማይ የዘለዓለም ሕይዎት እንደተዘጋጀላቸው ለቅዱስ ላሊበላ ቃል ኪዳን እንደተገባለትም ተናግረዋል። በተሰጠው ቃል ኪዳን ምክንያት የልደት በዓል በድምቀት እንደሚከበርም ገልጸዋል። ወደ ቅዱስ ላሊበላ የሚመጡ አማኞች ድንቅ ነገር ብቻ አይተው የሚመለሱ ሳይኾን በረከትን በስጋም ኾነ በነፍስ የሚያገኙበት፣ በማያልፍ እና በማይሻር ቃሉ የተሰጠውን ቃል ኪዳን የሚካፈሉበት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ አያሌ ፈተናዎች በገጠሟት ጊዜም የልደት በዓል በላሊበላ መከበሩ እንዳልተቋረጠ ነው የተናገሩት። በዓለ ልደቱ በላሊበላ አይስተጓጎልም ብለዋል። እንደ ቀደመው ጊዜ ሁሉ ዘንድሮም የልደት በዓልን ለማክበር ወቅቱ የሚፈልገውን ዝግጅት ስለማድረጋቸውም አስገንዝበዋል። ቤተክርስቲያኗ እንግዶቿን እና ልጆቿን ለመቀበል ዝግጅቷን አጠናቃለች ነው ያሉት።
በረከት ለማግኘት ወደ ተቀደሰው ሥፍራ የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል በቤተክርስቲያን ሥርዓት መሠረት ዝግጅቱ መደረጉን ነው የተናገሩት። እየገቡ ያሉ እንግዶችንም በክብር እየተቀበሉ መኾናቸውንም ገልጸዋል። የቀደሙት አባቶች ኢትዮጵያን ዓለም እንዲያደንቅ፣ ዓለም እንዲመለከታት ያደረጉት በሥራቸው ብቻ አይደለም ያሉት አባ ሕርያቆስ ሰውንም ፈጣሪንም በማክበራቸው ነው ብለዋል።
ፍቅር ፈጣሪ ይወዳል በመኾኑም ሰዎች እርስ በርሳቸው እና ፈጣሪን በመውደድ ብሎም በማክበር መኖር አለባቸው ነው ያሉት። አባቶቻችን የሰጡንን ድንቅ የኾነውን፣ እግዚአብሔርም ወዶና ፈቅዶ የገለጠውን፣ የአባቶቻችን የመታዘዝ ምልክት የኾነውን ሥፍራ መጎብኘት እና በበዓሉ ተገኝቶ በረከት ማግኘት ጽድቅ ነው ብለዋል።
ኑ የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ አድንቁ፣ ከበረከቱም ተካፈሉ ነው ያሉት። በቅዱሱ ቦታ እንድትገኙ ጥሪ እናቀርብላችኋለንም ብለዋል። ሥፍራዎች ሁሉ የሚተዳደሩበት እና የሚታወቁበት የራሳቸው ጸጋ አላቸው ያሉት አባ ሕርያቆስ እንደ መታደል ኾኖ ላሊበላ እና አካባቢው የታደለው ጸጋ ለቱሪዝም ነው፤ ከዚህ ጸጋ የማይጠቀም የለም ብለዋል።
በተደጋጋሚ በተፈጠሩ ችግሮች የቱሪዝም እንቅስቃሴው ቀንሷል፣ ቱሪዝሙ በመቀነሱ ደግሞ ቤተክርስቲያኗ እና ነዋሪዎች ብዙ ነገር አጥተዋል ነው ያሉት። የቱሪዝም እንቅስቃሴው እንደ ቀደመው እንዲኾን፣ የተጎዳችው ቤተክርስቲያን እና የአካባቢው ማኅበረሰብ እንዲጠቀም እንግዶች ወደ ተቀደሰው ሥፍራ እንዲመጡም ጥሪ አቅርበዋል።
አባ ሕርያቆስ በመልዕክታቸው ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አማኞች እና ለመላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረሳችሁ ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!