
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ የልደት በዓልን ምክንያት በማድረግ ‘ጥርን በባሕር ዳር ባዛራችን ለሰላም የንግድ አውደ ርዕይ እና ባዛር’ እንደሚያካሂድ አስታውቋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ አደራ ጋሼ በከተማዋ ከታኅሣሥ 25 እስከ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ የሚቆየው የንግድ አውደ ርዕይ እና ባዛር አምራች እና ሸማቹን በማገናኘት የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ ያለመ መኾኑን ገልጸዋል።
ግብይት ለሚበዛበት የልደት በዓል አምራች እና ሸማችን ማገናኘት እንዲሁም ተቀዛቅዞ የነበረውን ምጣኔ ሐብት ለማነቃቃት ታሳቢ መደረጉንም ተናግረዋል። በባዛሩ ያለውን አንጻራዊ ሰላም የምናሳይበት ነውም ብለዋል አቶ አደራ።
ባዛሩ የሚካሄደው በባሕር ዳር ከተማ በተለምዶ አጠራሩ ”አለ በጅምላ” በሚባለው ቦታ ነው። በንግድ አውደ ርዕይ እና ባዛሩ የኢንዱስትሪ እና የግብርና ምርቶች እንዲኹም የእንስሳት እና የእንስሳት ተዋጽኦዎች ይቀርባሉ። የአቅራቢም ኾነ የሸማች መግቢያ በነጻ ነው ተብሏል።
ታህሳስ 25 ከእኩለ ቀን ተጀምሮ እስከ ሰኞ ድረስ የሚቆየው ይኾናል።
ያለ ደላላ ጣልቃ ገብነት አርሶ አደሮች፣ የኢንዱስትሪ አምራቾች እና ጅምላ አከፋፋዮች ስለሚገቡ ኅብረተሰቡ በርካሽ ዋጋ እንዲሸምት ጥሪ ቀርቧል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!