በክልሉ እየተሻሻለ የመጠውን የጸጥታ ሁኔታ ዘላቂ ለማድረግ እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ።

45

ደሴ: ታኅሣሥ 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ወሎ ዞን በወቅታዊ የሰላም እና ጸጥታ ተግባራት ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት በደሴ ከተማ እየተካሄደ ነው። በውይይቱ ላይ የክልል የዞን እና ከሁሉም ወረዳዎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።

የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ኮሚሽነር ደጀኔ ልመንህ በክልሉ በባለፈው ዓመት ከነበረው የጸጥታ ስጋት አንጻር አሁን ላይ ለውጥ መኖሩን ጠቅሰዋል። ከጸጥታ ኃይሉ ባሻገር ኀብረተሰቡ ለሰላሙ መጠበቅ እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ ለውጤቱ መገኘት ሚና እንደነበረው አመላክተዋል።
በክልሉ እየተሻሻለ የመጣውን የጸጥታ ሁኔታ ለማስቀጠል እየተሰራ መኾኑን ነው ምክትል ኀላፊው የገለጹት።

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዓሊ መኮንን በዞኑ ያለውን የሰላም ሁኔታ አስተማማኝ ለማድረግ የጸጥታ ኃይሉ ከሕዝቡ ጋር በመኾን ባከናወነው ሥራ አብዛኛውን ቀጣና የተረጋጋ ማድረግ ተችሏል ብለዋል። ለዚህ ውጤት የማኅበረሰቡ ሚና ከፍ ያለ እንደነበርም አመላክተዋል።

አሁን ላይ ኅብረተሰቡ ጽንፈኞችን በቃኝ ማለት ጀምሯል ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ራሱን በማደራጀት እየታገለ እንደሚገኝም ነው የገለጹት። ሕዝቡ በቀጣይም የሕግ የበላይነት መከበር አለበት የሚል አቋም ያለው በመኾኑ ይህንንም በማጠናከር በዞኑ ያለውን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ ይሠራል ነው ያሉት።

ዘጋቢ:- ተመስገን አሰፋ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየፈተና ጥሪ ማስታወቂያ !
Next article‘ጥርን በባሕር ዳር፤ ባዛራችን ለሰላም” የንግድ አውደ ርዕይ እና ባዛር ሊካሄድ ነው።