
ጎንደር: ታኅሣሥ 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥትን እና የሕዝብን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ ታጣቂዎች በሰራባ ተሐድሶ ማሰልጠኛ ማዕከል አቀባበል ተደርጎላቸዋል። የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎችም በሰራባ ማሰልጠኛ ማዕከል ተገኝተው አቀባበል አድርገዋል።
በአማራ ክልል ከአንድ ዓመት በላይ በዘለቀው ግጭት የክልሉ ሕዝብ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ ውስጥ ገብቶ ቆይቷል። ከዚህ ቀውስ በመውጣት ክልሉ ወደ ሰላም እንዲመጣ መንግሥት እና ሕዝብ ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎችን ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወሳል። የክልሉ ሕዝብ ወደ ነበረበት ሰላም መመለስ አለበት ያሉ ታጣቂዎችም ይህን የሰላም ጥሪ በመቀበል በተሐድሶ ማዕከላት አቀባበል እየተደረገላቸው ይገኛል።
አስተያየታቸውን የሰጡት በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሰራባ ካምፕ አቀባበል የተደረገላቸው አላምረው ንጉሴ እና አማኑኤል ተካልኝ የክልሉ ሕዝብ በዚህ ግጭት ያተረፈው ሞት እና ውድመት መኾኑን በመረዳታቸው የመንግሥትን እና የሕዝብን ጥሪ መቀበላቸውን ተናግረዋል። የገቡበት የትጥቅ ትግል ስህተት እንደነበር የገለጹት የመንግሥትን ጥሪ የተቀበሉት ታጣቂዎች የበደልነውን ሕዝብ ለመካስ ዝግጁ ነን ብለዋል።
በክልሉ ያለው ቀውስ መቆም እንዳለበት ያነሱት ወርቅየ ሀድጎ እና ሰለሞን አስማረ በጦርነት የሚመጣ ለውጥ እንደሌለ ባለፉት ጊዜያት ታዝበናል ብለዋል። በዚህ የትጥቅ ትግል የምናተርፈው ነገር የለም የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ በጫካ የሚገኙ ወንድሞቻችንም የመንግሥት ጥሪውን እንዲቀበሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በአቀባበሉ ላይ የተገኙት የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች በበኩላቸው የክልሉን ሕዝብ ሰላም ለማድረግ የመንግሥትን እና የሕዝብን ጥሪ መቀበላችው የሚመሰገን ነው ብለዋል። በቀጣይም የክልሉን ሕዝብ ወደ ሰላም እንዲመጣና ወደ ቀደመ ልማቱ እንዲመለስ የራሳችሁን ኀላፊነት ልትወጡ ይገባል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የሰላም ጥሪን የተቀበሉ የታጠቁ ኃይሎች በጭልጋ ሰራባ ካምፕ ትጥቃቸውን ለመንግሥት ማስረከባቸውን የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ በሪሁን መንግሥቱ ገልጸዋል። መንግሥት እና የክልሉ ሕዝብ የሚያቀርበውን የሰላም ጥሪ እየተቀበሉ የሚገኙ ኃይሎች የክልሉን ሕዝብ ልማት ለማሳደግ እንዲሠሩ ስልጠና እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።
አቶ በሪሁን የታጠቁ ኃይሎች የሰላም ጥሪውን መቀበላቸው የክልሉ ሕዝብ ሰላም እንዲረጋገጥ ያደርጋል ነው ያሉት። የሰላም ጥሪውን ተቀብለው የገቡ ታጣቂዎች ከስልጠና በኋላ የሥራ እድል እንደሚፈጠርላቸውም አስታውቀዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!