“በትህትና ዝቅ ይላሉ፤ በክብር ከፍ ብለው ይኖራሉ”

45

ወልድያ: ታኅሣሥ 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ትሁቶች ናቸውና በትህትና ዝቅ ይላሉ። ደጎች ናቸውና በደግነት ይኖራሉ። እንግዳ ተቀባዮች ናቸውና ቤታቸውን ከፍተው እንግዳ ይቀበላሉ። ስሞት አፈር ስኾን እያሉ ያጎርሳሉ፣ ከጠራ ውኃ እየቀዱ የተጠሙትን ያጠጣሉ፣ የተራቡትን እየቆረሱ ያጎርሳሉ። የደከሙትን ያሳርፋሉ። መንገድ የጠፋባቸውን መንገድ ያሳያሉ።

የአባቶቻቸውን ባሕል ይጠብቃሉ። ሃይማኖታቸውን ያጸናሉ። ታሪካቸውን ከእነ ክብሩ ያኖራሉ። በአበው ብሂልና ወግ በትህትና ዝቅ ዝቅ ይላሉ። ለአበው በተሰጠ ክብርም ከፍ ከፍ ይላሉ። በዚያች ምድር ታሪክ እና ሃይማኖት ከብረው ይኖራሉ። እሴት እና ባሕል ከእነ ሞገሳቸው ይገኛሉ። የጥንቱን ሳይረሱ፣ ሕግና ሥርዓቱን ሳይጥሱ፣ የቀደመውን ሳያፋልሱ ይዘው ዘልቀዋል። ምድሯ እንደ አብርሃም ቤት እንግዳ የማይጠፋባት፣ በሰርክ እንግዳ የሚገባባትና የሚወጣባት፣ አመስግኖ መሸኘት፣ እግር አጥቦ መቀበል ባሕል የኾነባት፣ በእንግዳ በረከት የሚኖርባት ናት።

ንግሥናን እና ቅድስና በአንድነት የተሰጡት፣ የመናገሻ ዙፋኑን፣ የቅድስና መንበሩን ይዘው የኖሩት፣ የረቀቀ ነገርን በምድር የሠሩት፣ ለሰማዩም ቤታቸው በምድር በተጋድሎ የበረቱት፣ የተወደደውን የፈጸሙት ቅዱሳን ነገሥታት የኖሩባት፣ የተመላለሱባት፣ ሕግ እና ሥርዓት ያጸኑባት፣ አያሌ ታሪክን የሠሩባት ናት ቀደምቷ ሮሐ። የአሁኗ ላሊበላ።

ይህች ሥፍራ በቤተ ክህነቱም በቤተ መንግሥቱም ታሪክ ጎልታ ትነሳለች። እንግዶች የሚበዙባት፣ እንግዳ ተቀባዮች የሚኖሩባት ናት። ላሊበላ ዓለም የተደነቀባቸውን ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን የያዘች፣ ከጥበብም የረቀቀውን ጥበብ የታደለች ናትና እንግዶች ያዩዋት ዘንድ ይወዷታል። ከሩቅም ከቅርብ እየተነሱ ይከትሙባታል። ይህች ሥፍራ በኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት ደግሞ በእንግዶች ትሞላለች። በረከትን ብለው በአራቱም አቅጣጫ በሚመጡ አማኞ ትከብባለች። ታሪክን እና ሃይማኖትን፣ ጥበብ እና የጥበብ ውጤትን ለማየት የሚመጡ ተጓዦችን ትቀበላለች።

በዓለ ልደት ከመድረሱ አስቀድሞ አማኞች እና ተጓዦች ወደ ላሊበላ ይገሰግሳሉ። በተቀደሰው ሥፍራ ለመድረስም ይፋጠናሉ። በላሊበላ በደረሱም ጊዜ ደጋጎቹ እና ትሁታኑ የላሊበላ ከተማ ነዋሪዎች እንኳን መጣችሁ እያሉ እጅ እየነሱ ሰላምታ ይሰጧቸዋል፣ ዝቅ ብለው ያከብሯቸዋል፣ ከእግራቸው ሥር ተቀምጠው እግራቸውን እያጠቡ ፍቅርን ይሰጧቸዋል። ደግነትን ያሳዩዋቸዋል።

እነኾ በዓለ ልደት እየደረሰ ነው። በየብስም በአየርም የሚገሰግሱ እንግዶች ወደ ላሊበላ እየገቡ ነው። የላሊበላ ነዋሪዎችም ከትናንት ጥንት፣ ከዛሬ በፊት ትናንት ሲያደርጉት እንደነበረው ሁሉ እንግዶችን እግራቸውን እያጠቡ እየተቀበሏቸው፣ የደከሙትን እያሳረፏቸው፣ የዛሉትን እያበረቷቸው፣ የተጠሙትን እያጠጧቸው ነው። እግር አጥቦ መቀበል የቆየች እሴታቸው፣ የትህትና መግለጫቸው ናትና።

በረከት ለማግኘት ለቀናት ተጉዘው አማኞች በረጅም ጉዞ የደከመው ጉልበታችን ላሊበላ በገባን ጊዜ ጠነከረ። ለምን ካላችሁን ስንገባ እግር እያጠቡ፣ እያበሉ እያጠጡ ስለ ተቀበሉን ነው ይላሉ። ከእግራችን ሥር እየተቀመጡ ሲያጥቡን ድካሙ ለቀቀን። ታሪኩ መነገር ያለበት ሀገር፣ የደግ ሀገር ነው ብለዋል።

ወደ ከተማ ሲገቡ እግራቸውን የሚያጥባቸው፣ ውኃ የሚያቀብላቸው፣ የሚበላም የሚሰጣቸው ብዙ እንደኾነ ነው የተናገሩት። ተጓዦቹ ላሊበላ ከመድረሳቸው አስቀድሞም በየመንገዱ ለበረከት እያሉ እግራቸውን የሚያጥባቸው፣ ጓዛቸውን እየተሸከመ የሚሸኛቸው ብዙ እንደነበር ነው የነገሩን። የላሊበላ ከተማ ነዋሪዎች ዕውነትም የቅዱሱ በረከት ያለባቸው ናቸው ይላሉ።

የላሊበላ ወጣቶች ተስፋ በጎ አድራጎት ማኅበር ሠብሣቢ አንዱዓለም ደሳለኝ እንግዶች ከከተማዋ ከመግባታቸው አስቀድሞ ከከተማ እየወጡ እየሄዱ እንደሚቀበሏቸው ነው የሚናገረው። ከከተማ ውጭ ሄደን ጓዛቸውን ተሸክመን ይዘናቸው እንመጣለን። ከተማ በደረሱ ጊዜም እግራቸውን እናጥባለን። ከከተማዋ ነዋሪዎች የተቀበልነውን ምግብ እና መጠጥም ለእንግዶች እንሰጣለን ነው የሚለው።

የደከማቸውን ሰዎች እናግዛለን፣ ይሄ ከአባቶቻችን የተቀበልነው ባሕል ነው። እኛም እንደ አባቶቻችን እናደርጋለን። ይህ ባሕላችን ነው። እግር ማጠብ በረከታችን ነው። የቅዱስ እና የንጉሥ ልጆች ስለኾን የምንኖረው በበረከት ነው። እንግዳ መቀበልን፣ ፍቅርን፣ አንድነትን የተማርነው ከአባቶቻችን ነው ብሏል።

የላሊበላ ወጣቶች ተስፋ በጎ አድራጎት ማኅበር ገንዘብ ያዥ ገነት አለልኝ እንግዶች ሲመጡ ሸክማቸውን እየተቀበልን፣ እግራቸውን እያጠብን እናስተናግዳለን፣ ይህ ለእኛ ረድኤት ነው። በዚህ ረድኤትም እንኖራለን ብላለች። ከታዳጊዎች እስከ ታላላቅ ሰዎች ድረስ እግር እናጥባለን። ይህ ለእኛ ትልቅ በረከት እና ጸጋ ነው። ምክንያቱም ለጽድቅ እና ለበረከት በሚመጡ ሰዎች እንመረቃለንና ነው የምትለው። የላሊበላ ወጣቶች ከአበው ለቆየች እሴት፣ ሃይማኖት፣ በረከት እና ምርቃት ታላቅ ክብር አላቸው።

እንደከተማዋ ነዋሪዎች ሁሉ የእንግዶችን እግር ሲያጥቡ ያገኘናቸው የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ወንድምነው ወዳጅ የልደትን በዓል ለማክበር እንግዶች እየገቡ ነው ብለዋል። ከተማ አሥተዳደሩ ቅድመ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን ነው የተናገሩት። ቀኑ እስኪደርስ ድረስ ሲጓጉላቸው የነበሩ እንግዶችን ቀኑ ደርሶ እየተቀበልን ነው ብለዋል።

በርካታ እንግዶች ወደ ከተማችን እየገቡ ነው። እንግዶችንም በተለመደ የእንግዳ አቀባበል ባሕላችን እየተቀበልን ነው ይላሉ። በተለይም ወጣቶች እንግዶችን እግራቸውን እያጠቡ፣ የከተማዋ ነዋሪዎችም ምግብ ለእንግዶች እየሰጡ እየተቀበሏቸው ነው ብለውናል። የተራበውን የማብላት፣ የተጠማውን የማጠጣት፣ የደከመውን የማበርታት ባሕል በላሊበላ አይቋረጥም። ይህ ባሕል ሁልጊዜም በስስት የሚጠበቅ፣ እንግዶቻችንን በክብር የምንቀበልበት ነው ይላሉ። በየትኛውም አካባቢ የሚገኙ እንግዶች ቢመጡ በክብር ተቀብለን በፍቅር እንሸኛቸዋለን ነው ያሉት። እንግዶች የልደት በዓልን በታላቁ ሥፍራ ከእንግዳ ተቀባዩ ሕዝብ ጋር እንዲያከብሩም ጥሪ አቅርበዋል።

ላሊበላ እንግዳ በስስት የሚጠበቅባት፤ በፍቅር የሚከተምባት፤ በደስታ የሚቆይባት፤ በናፍቆት የሚሸኝባት ናት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ4 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች ወደ ሥራ መግባታቸውን የወልድያ ከተማ ኢንቨስትመንት መምሪያ አስታወቀ።
Next articleየመንግሥትን እና የሕዝብን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ ታጣቂዎች በሰራባ ተሐድሶ ማሰልጠኛ ማዕከል አቀባበል ተደረገላቸው።