
ወልድያ: ታኅሣሥ 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የወልድያ ከተማ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ዮሐንስ ገበያው በአምራች ኢንዱስትሪ እና በአገልግሎት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ 60 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ አውጥተው ወደ ሥራ ግብተዋል ብለዋል። ከእነዚህ ውስጥ 11 ባለሃብቶች በአግባቡ ማሽን አስገብተው ማምረት መጀመራቸውን ነው ያስረዱት።
378 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ በማውጣት እና በማሳደስ ለማልማት በዝግጅት ላይ ናቸው ብለዋል። ባለሃብቱ በእንስሳት እርባታ፣ በእንስሳት ተዋጽኦ ማቀነባበር፣ በኮንስትራክሽን ዘርፍ፣ በሆቴል ቱሪዝም ዘርፍ እና በሕክምና ዘርፍ የተሰማሩባ ናቸው። እነዚህ ባለሃብቶች በጥቅሉ ከ4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል አስመዝግበዋል ብለዋል።
አልሚ ባለሃብቶቹ ለ52 ሺህ 992 ሰዎች በቋሚ እና በጊዜያዊነት የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ ተብሏል። ምርት መስጠት የጀመሩት የኢንቨስትመንት ተቋማት ለ5 ሺህ 351 ሰዎች ቋሚ እና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን የመምሪያው ኀላፊ ነግረውናል። የወልድያ ከተማ ለኢንቨስትመንት ምቹ ነው ያሉት ኀላፊው ከተማዋ ከጅቡቲ 535 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መገኘቷ የገቢ እና ወጭ ንግድን ያቀላጥፋል ብለዋል።
በተጨማሪም የአዋሽ-ወልድያ ሀራ ገበያ የባቡር መስመር ለገቢ እና ወጭ ንግድ ምቹ በመኾኑ ኢንቨስተሮች በከተማዋ እንዲያለሙ ጥሪ አቅርበዋል። ለዚህም በከተማዋ ማስተር ፕላን መሠረት ከ2 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በንድፍ ፕላን የተመላከተ የኢንቨስትመንት ቦታ ተዘጋጅቷል፤ 37 ነጥብ 1 ሄክታር ደግሞ ሳይት ፕላን ተዘጋጅቶለት ኢንቨስተሮቸን እየጠበቀ ነው ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!