
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ ታሪክ እና ይዘቱን ጠብቆ የታደሰውን ብሔራዊ ቤተመንግሥት አስመልክተው መልእክት አስተላልፈዋል። በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት “ብሔራዊ ቤተ መንግሥት የኢትዮጵያ ትናንት፣ ዛሬና ነገ የተገናኙበት አማካይ ሥፍራ ነው” ብለዋል።
በሕዝብና በመንግሥት መካከል መቀራረብ፣ መነጋገር፣ መግባባት እንጂ በግንብ የተከለለ የፖለቲካ ሕይወት አያስፈልግም፤ የቤተ መንግሥቱ ለሕዝብ ክፍት መሆንም የዚህ አዲስ የፖለቲካ ዕሳቤያችን ሁነኛ ትእምርት ነው ሲሉም ገልጸውታል።
ዛሬ ከሚዲያ፣ ከቱሪዝም አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ባለሞያዎች ጋር ታሪኩን ጠብቆ በፍጥነት እና በጥራት በታደሰው በዚህ ዕጹብ ድንቅ ሥፍራ አሳልፈናል ብለዋል፡፡
ብሔራዊ ቤተ መንግሥት የኢትዮጵያን ዘመናዊ የመንግሥትነት ታሪክ ለዛሬውና ለነገው ትውልድ ገልጠው ከሚያሳዩ እና ከሚያስተምሩ ውድ ቅርስና ሀብቶቻችን አንዱ ስለመኾኑም አመላክተዋል።
ቤተ መንግሥቱ የትናንት ድሎቻችን እና የውጣ ውረድ ታሪካችን መዝገብ፣ የዛሬ የማንሰራራት ዘመናችን መነሻ ወረታችን፣ የነገ ራዕያችንና የመሻታችን ማሳያም ነው ሲሉም አብራርተዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!