የደብረ ማርቆስ ከተማን የንጹህ መጠጥ ውኃ ተደራሽነት ለማሳደግ እየተሠራ ነው።

41

ደብረ ማርቆስ: ታኅሣሥ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ማርቆስ ከተማ የመጠጥ ውኃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት የከተማውን የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ችግር ለመፍታት ከማኅበረሰቡ እና ከምሥራቅ ጎጃም ዞን ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።

የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር የመጠጥ ውኃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ መንግሥቱ ተፈራ ለውኃ ተቋማት የሚደረገው ጥበቃ እና እንክብካቤ አነስተኛ ከመኾኑ ጋር ተያይዞ ነባር የውኃ ምንጮች ጉዳት እየደረሰባቸው መኾኑን አንስተዋል ።

የከተማውን የውኃ ችግር በጊዜያዊነት ከመፍታት ጎን ለጎን የራስን አቅም አሟጦ በመጠቀም ዘላቂ መፍትሔ መስጠት ተገቢ ነው ብለዋል። የደብረ ማርቆስ ከተማ የውኃ ሽፋን 29 በመቶ ላይ እንደሚገኝ የጠቆሙት የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ በውኃ አቅርቦት እና ፍላጎት መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት ለማጥበብ የኅብረተሰቡ እና የባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ መኾኑን ገልጸዋል።

አሳሳቢ እየኾነ የመጣውን የንጹህ መጠጥ ውኃ ችግር ለማቃለል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ዝግጁ መኾናቸውን የተናገሩት የከተማዋ ነዋሪዎች የውሃ እጥረቱ በዘላቂነት መፍትሔ እንዲያገኝ በከተማው የሚገኙ ተቋማት እና ድርጅቶች የበኩላቸውን ኀላፊነት እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ ዋለ አባተ የደብረ ማርቆስ ከተማን የንጹህ መጠጥ ውኃ ተደራሽነት ችግር ለመፍታት የቁሳቁስ እና ሙያዊ ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል። በውኃ መገኛ አካባቢዎች ተፋሰሶችን በማልማት ያለውን የውኃ ችግር ለመፍታት እና በውኃ ተቋማት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እንሠራለን ብለዋል።

የደብረ ማርቆስ ከተማ የመጠጥ ውኃ እጥረትን ለመፍታት ከተቀመጡ ጊዜያዊ መፍትሔዎች በተጨማሪ ለዘላቂ መፍትሔ መሥራት አስፈላጊ መኾኑን በአፅንኦት አንስተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article25 በመቶ የመተንፈሻ ህመም የሚመጣው እጅን በአግባቡ ባለመታጠብ ነው።
Next article“ብሔራዊ ቤተ መንግሥት የኢትዮጵያ ትናንት፣ ዛሬና ነገ የተገናኙበት አማካይ ሥፍራ ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ