25 በመቶ የመተንፈሻ ህመም የሚመጣው እጅን በአግባቡ ባለመታጠብ ነው።

30

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የእጅ መታጠብ ቀን “ንጹሕ እጆች ለጤናችን ዋስትና ናቸው” በሚል መሪ መልዕክት በባሕር ዳር ከተማ እየተከበረ ነው። በበዓሉ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ የክልሉ ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ እጅን መታጠብ በጤናው ሴክተር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተተገበረ ይገኛል ብለዋል።

ንጽሕናን በመጠበቅ ራስን ከተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች መጠበቅ እንደሚገባም ተናግረዋል። ቀኑ ሲከበር ከግለሰብ እስከ ማኅበረሰብ እጅን ባለመታጠብ ሊከሰቱ የሚችሉ በሽታዎችን በማስገንዘብ እና ሁሉም ለግል ንጽህና ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ በማሰብ ነው ብለዋል። በንጽሕና ጉድለት የሚመጡ በሽታዎችን መከላከል ከሚቻልባቸው መንገዶች ውስጥ እጅን በአግባቡ መታጠብ እንደኾነም ገልጸዋል።

ትራኮማን መከላከል የሚቻለው እጅን በሚገባ በመታጠብ እንደኾነም ቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል። ንጽሕና የአንድ ቀን ጉዳይ ብቻ መኾን እንደሌለበትም አንስተዋል። በክልሉ ጤና ቢሮ የሐይጅን እና የአካባቢ ጤና አጠባበቅ ቡድን መሪ ሳሙዔል ካህሊ እጅን አለመታጠብ ለተቅማጥ በሽታ ይዳርጋል፤ በተለይም 25 በመቶ የመተንፈሻ ህመም የሚመጣው እጅን በአግባቡ ባለመታጠብ እንደኾነ ተናግረዋል።

ያልታጠበ እጅ ለባክቴሪያ፣ ለጀርም እና ቫይረስ መራቢያ በመኾኑ እጅን በመታጠብ ራስን ከበሽታ በቀላሉ መጠበቅ ግድ ይላል ነው ያሉት። ቡድን መሪው እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2030 ጽዱ ኢትዮጵያን ለመፍጠር እየተሠራም እንደኾነ ገልጸዋል። ለዚህም በፓይለት መርሐ ግብር የተመረጡ ወረዳዎች መኖራቸውን ቡድን መሪው ተናግረዋል።10 በመቶ የጤና ተቋማትንም በዚህ ዓመት ጽዱ ለማድረግ ሥራው ተጀምሯል ነው ያሉት።

በ2030 ሜዳ ላይ መጸዳዳትን ዜሮ ለማድረግ እንቅስቃሴው ተጀምሯልም ብለዋል። በቀሪ ስድስት ዓመታት ውስጥ መሠረታዊ የእጅ መታጠቢያ ቁሶችን መቶ በመቶ ለማሟላት በዕቅድ ተይዞ ወደ ሥራ ተገብቷል ነው ያሉት። ኅብረተሰቡም ለንጽህና ትኩረት እንድሰጥ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ተግተው እየሠሩ ይገኛሉ።

የእጅ መታጠብ ቀን በባሕር ዳር ከተማ ሲከበር ተሳታፊ የነበሩት በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ የግል እና የአካባቢ ጤና አጠባበቅ ኦፊሰር ዳንኤል ይትባረክ “በእኛ አካባቢ የእጅ መታጠብ ልምዱ ዝቅተኛ ስለኾነ መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል። የባሕርይ ለውጥ ለማምጣትም የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል” ነው ያሉት።

ተማሪ ቤተልሔም በለጠ ዕለቱን ከማክበር ባለፈ በርካታ ሰዎች በሚሰባሰቡበት አካባቢዎች ትምህርቱን ሳይቆራረጥ በመስጠት ለውጥ ማምጣት ይቻላል ባይ ናት። ሌላው አስተያየት ሰጭ መዝገቡ ሙሉቀን እጅን መታጠብ እና በመጸዳጅያ ቤት መጠቀምን ልምድ ለማድረግ ማኅበረሰቡን ማሳተፍ ተገቢ ነው ይላሉ።

የእጅ መታጠብ ቀን በዓለም ለ16ኛ በኢትዮጵያ ደግም ለ15ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለፈረንጆቹ አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።
Next articleየደብረ ማርቆስ ከተማን የንጹህ መጠጥ ውኃ ተደራሽነት ለማሳደግ እየተሠራ ነው።