
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ለሠራተኞች የአቅም ግንባታ ሥልጠና እየሠጠ ነው። የክልሉን የንጹህ መጠጥ ውኃ እና የኢነርጂ አቅርቦት ለማሳደግ እና የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመሥጠት ለሠራተኛው የአቅም ግንባታ ሥልጠና መሥጠት ማስፈለጉን የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ኀላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ/ር) ገልጸዋል። ሥልጠናው ለአራት ቀናት የሚቆይ ነው።
የተቀመጡ ዕቅዶችን የመፈጸም አቅም ማጎልበት እና ተቋሙ የጀመረውን የሪፎርም ሥራ በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ በዘመናዊ መንገድ አገልግሎት ለመሥጠት የሚያግዝ ነው ተብሏል።
ከዚህ ባለፈ ፕሮጀክቶች ከተገነቡ በኋላ ዘላቂ አገልግሎት እንዲሰጡ፣ የመልካም አሥተዳደር ችግር ያለባቸውን ፕሮጀክቶች ደግሞ ጉድለታቸውን ለመሙላት አቅም እንደሚኾን ኀላፊው ገልጸዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት በንጹህ መጠጥ ውኃ እና በኀይል አማራጭ በፕሮጀክት ሥራዎች ላይ ማኅበረሰቡን ባሳተፈ መንገድ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራ ቢሮ ኀላፊው ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!