
ደሴ: ታኅሣሥ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሰልፍ ኸልፕ አፍሪካን የተባለ መንግሥታዊ ያልኾነ ድርጅት ከዓለም የምግብ ፕሮግራም ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ለበጋ መስኖ የሚኾን የምርጥ ዘር ለደቡብ ወሎ ዞን ድጋፍ አድርጓል። የሰልፍ ኸልፕ አፍሪካ የምሥራቅ አማራ አስተባባሪ ቸኮለ ወልዴ ድርጅቱ የግብርና ዘርፉን ለመደገፍ ሢሠራ መቆየቱን ገልጸዋል።
አሁን ላይ ደግሞ ለበጋ መስኖ ስንዴ ሥራ እንዲኾን የስንዴ ምርጥ ዘር ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል። ድርጅቱ ከ25 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ በአማራ ክልል ለሚገኙ 16 ወረዳዎች ከሦስት ሺህ ኩንታል በላይ የምርጥ ዘር ስንዴ ድጋፍ እንዳደረገ አብራርተዋል። ከተደረገው ድጋፍ ውስጥ 1ሺህ 949 ኩንታሉን ለደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ማስረከባቸውን ነው የተናገሩት።
በዞኑ ለሚገኙ የበጋ መስኖ ተጠቃሚ 10 ወረዳዎች ተደራሽ እንደሚኾንም ነው አስተባባሪው የገለጹት። በርክክቡ ላይ የተገኙት የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ አህመድ ጋሎ በዞኑ ከ36 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ እና በበልግ ዝናብ ለማምረት ማቀዳቸውን ገልጸዋል።
በዚህም ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ነው የተናገሩት።
ሰልፍ ኸልፕ አፍሪካም የመስኖ ልማት ሥራውን ለመደገፍ ያደረገው የምርጥ ዘር ድጋፍ ለውጤታማነቱ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመላክተዋል። ድጋፉ የመስኖ እና የበጋ መስኖ ልማት ተጠቃሚ በኾኑ ወረዳዎች ለሚገኙ አርሶአደሮች እንደሚሰራጭም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ተመስገን አሰፋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!