
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሥራየ ይናገር እንጅ እኔ በየሚድያው አልናገርም የሚለው በሳል ጸሐፊ አሌክስ አብርሐም ለንባብ የተለየ አቋም ያለው የጥበብ ሰው ነው። በአንድ ወቅት ከጋዜጠኛ ሰይፍ ፈንታሁን ጋር ባደረጋት ብቸኛ የሚድያ ንግግር ላይ ይህን ብሎ ነበር። አንድ ነገር ላይ ለምን እና እንዴት የሚል፣ የሚያንሰላስል አዕምሮ ባለቤት ለመኾን መፍትሔው ማንበብ ነው።
ለአብነት ብሎ የጀግንነት መገለጫው ከእውነት ጋር መቆም ነው ይላል። እውነትን ማረጋገጥ የሚቻለው ደግሞ ከማንበብ ነው የሚል ፍልስፍና እንዳለውም ሲናገር ሰምቸዋለሁ። ወጣቱ ትውልድ በነገሮች ላይ ስሜታዊ ሲኾን አየዋለሁ፤ ከዚህ ለመውጣት ግን ማንበብ ላይ መዝመት ይኖርብናል ብሎ ነበር።
እኔ በግሌ የአሌክስ አብርሐም ሐሳብ መልካም ነበር እላለሁ። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ታዲያ ንባብ ላይ ያለኝን ትዝብት ማካፈል ወደድኩ።
ትዝብቴ እራሴንም ይጨምራል። “ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል” የሚለውን ብሒል አብዛኛው ሰው ያውቀዋል ብየ አስባለሁ። ባይኾን አባባሉን ተረድተን አብዛኞቻችን አንባቢዎች ነን ወይ? የሚለው ላይ ግን እጠራጠራለሁ። በርግጥ በሀገራችን መጻፍ እና ማንበብን የሕይዎታቸው አንድ አካል ያደረጉ ስለመኖራቸው በሙሉ ልብ መናገር እችላለሁ። የሀገር ሥልጣን ይዘው እንኳ የሥራ ብዛት ሳይበግራቸው ውስጣቸውን በብዕራቸው የሚያናግሩ እንደነ ክቡር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ እና በአሉ ግርማ ዓይነት ጦማሪዎች የነበሩባት ሀገር ዜጎች ነን።
ለአብነት እውቅ የነበሩተትን አነሳሁ እጅ በርካታ የሥነ ጽሁፍ ጠበብቶችም ያሉባት ሀገር ውስጥ እንዳለንም እረዳለሁ። እንደ ሕዝብ እና ማኅበረሰብ ስመለከት ግን ለብዙዎቻችን ማንበብ ምንም አንዳልኾነ ተደርጎ እንደሚታይ እገነዘባለሁ። የማንበብን ጥቅም የምንረዳ ብንኖርም እንኳ በተግባር የምንተረጉም ስንቶቻችን ነን? ለንባብ ትርፍ ስዓት የለኝም፣ አመች ቦታ የለኝም፣ መጽሐፍ አላገኝም እያልን ምክንያት የምንደረድርስ የለንም? ሌላው ይቅርና ማንበብ የፋራ ነው እያልን ማንበብን በአሉቧልታ የምንደልልስ አንኖርም? ይህን ለእናንተ ለውድ አንባቢዎቼ እተወዋለሁ።
ይህን ርዕስ ጉዳይ በትዝብት እንዳነሳ ያነሳሳኝን አንድ ገጠመኘን ላንሳ። በባሕር ዳር ከተማ ዘንባባ መናፈሻ ከጓደኛየ ጋር ለመዝናናት ወደ ቦታው አመራን። ስለእውነት ለመናገር ዘንባባ መናፈሻ የጣናን ውብ ተፈጥሮ ተንተርሶ የተዘጋጀ በመኾኑ መልካም የመዝናኛ አካባቢ ኾኗል። ዘንባባ መናፈሻ በቅርብ የተደረገለት እድሳትም ተፈጥሮን አገናዝቦ የተሠራ በመኾኑ ጥሩ እረፍትን የሚያጎናጽፍ ቦታ ኾኖ አግኝቼዋለሁ። አረንጓዴ ሳሩ፣ እድሜ ጠገብ ዛፎቹ፣ በየመሐሉ የተሠሩ መዝናኛዎች፣ በአጠቃላይ ሁለ ነገሩ ሳቢ ኾኗል። እንደዚህ ዓይነት አካባቢዎች ቢበዙ ብየም ተመኝቻለሁ።
በዕለቱም በርካቶች ከወዳጆቻቸው ጋር ዘና ፈታ እያሉበት እንደነበር ከምወደው ከጓደኛየ ጋር ተመልክተናል። በተዝናኖቱ ወጣቶች ይበዙ ነበር። ከዚያ ሁሉ ሰው አልፎ ታድያ የኔ እና የጓደኛየ ዐይን አንድ ነገር አስተዋለ። አንድ የውጭ ሀገር ዜጋ ብቻውን ንጹህ አየሩርን ይኮመኩማል። ይህ የውጭ ሀገር ዜጋ ከሌሎች የተለየብን በአንድ ነገር ነው። ሌሎች የሀገሬ ሰዎች ሦስት እና አራት ኾነው ወሬውን እና ጨዋታውን ይሉታል። የሱ ጓደኛው ግን መጽሐፍ ብቻ ነበር።
እኔን እና ጓደኛየን የገረመን ታድያ የሱ በዚያ ቦታ መጽሐፍትን ጓደኛ ማድረጉ አይደለም። እራሳችን እንድንጠይቅ ያደረገን ከዚያ የውጭ ዜጋ በስተቀር ያሉ ወጣቶች ላይ አንድ እንኳን መጽሐፍ የያዘ ማጣታችን በዕለቱ ቆም ብለን እንድናስብ ያደረገን ነበር። እንዴት? ንባብ በግለሰብም ኾነ በማኅበረሰብ ሕይዎት ውስጥ ትልቅ ቦታ ሊኖረው የሚገባ መሠረታዊ ክህሎት ነው። የሰው ልጅ ስብዕናውን የሚቀርጽበት እና የማንነቱ መገለጫ የኮኑትን ባሕላዊ፣ ትረካዊ እና ሥነ-ጥበባዊ ቅርሶቹ፣ እሴቶቹ እንዳይጠፍ ፣ ለቀጣዩ ትውልድም ጠብቆ የሚያቆይበት፣ የሚያስተላልፍበትም ዓይነተኛ መሣሪያ ነው ብየ አስባለሁ።
የማያነብ ሰው ስለ ሕይዎት እና ስለ ተፈጥሮ፣ ስለ አካባቢያዊ እና ዓለም ዓቀፋዊ ሁነቶች ያለው ግንዛቤ ውስን እና የተዛባ የመኾን እድሉ የሰፋ ይኾናል ሲል አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ አንብቤ ነበር። የዳበረ የንባብ ልምድ ሲኖረን በቋንቋ የመጠቀም ብቃታችን ከማሳደጉም በላይ የዳበረ አስተሳሰብ እና ሚዛናዊ ግንዛቤ እንዲኖረን ያደርጋል። ታላላቅ ሳይንቲስቶች እና መሐንዲሶች፣ ስመ ጥር ደራሲያን፣ ጸሐፌ ተውኔቶች፣ ሰዓሊያን፣ ገጣሚያን እና ባለቅኔዎች እና ሌሎችም የሚፈጠሩት በዳበረ ንባብ ነው።
ይህን ታሳቢ ያደረገ የንባብ ልምድን ማዳበር ላይ ያለው ባሕላችን መፈተሽ ያለበት እንደኾነ ይሰማኛል። ሌላው ቢቀር እንኳ የሚያነቡ ሰዎችን ሥንቶቻችን እናበረታታለን? እኔ ግን መጽሐፍ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ሰዎችን ጉረኛ ማለት እና ሌሎች ስሞችን የሚሰጡ እንዳሉም ታዝቤያለሁ።
የንባብ ክሕሎትን ለማዳበር ከሚያግዙ ስልቶች ውስጥ ብዙዎች የሚመክሩት በሄዱበት ሁሉ መጽሐፍትን ይዞ መንቀሳቀስ አንዱ ነው። ይህ ኾኖ ሳለ እኛ በተቃራኒው ከቆምን አንባቢ ትውልድን እንዴት ማፍራት እንችላለን? እያንዳንዳችን ኀላፊነትስ የለብንም? በተለይ አሁን አሁን ደግሞ የማኅበራዊ ሚድያ ላይ ተጥዶ መዋል ንባብ ጨርሶ እንድረሳ ሊያደርገውም ይችላል የሚል የራሴ ዕይታ አለኝ። ስለዚህ በኔ አመለካከት ራስን መመልከቻ እና ሚዛን የኾነው የንባብ ባሕል ላይ ትኩረት ልናደርግ ይገባል እላለሁ! ሰላም።
ዘጋቢ: ሰለሞን አንዳርጌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!