በበዓል ምክንያት ወደ ላሊበላ እና ጎንደር ከተማ የሚያደርገውን በረራ እንደሚያሳድግ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ገለጸ።

46

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመጭዎቹ ሳምንታት የሚከበሩትን የገና እና የጥምቀት በዓላትን አስመልክቶ የደንበኞችን ፍላጎት መሠረት በማድረግ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ ውቅር አብያተ ክርስትያናት ወደሚገኙበት ላሊበላ እና ጎንደር ከተማ የሚያደርገውን በረራ እንደሚያሳድግ ገልጿል።

አየር መንገዱ ወደ ከተሞቹ ከሚያደርገው መደበኛ ዕለታዊ በረራ በተጨማሪ ሌሎች በረራዎችን በመመደብ በዓላቱ በድምቀት እንዲከበሩ ሀገራዊ ኀላፊነቱን ለመወጣት ዝግጁ መኾኑን ነው በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ያብራራው።

አካባቢዎቹ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚመጡ ጎብኝዎች በስፋት የሚታደሙባቸው በመኾናቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአየር በረራን በበቂ ሁኔታ በማቅረብ የተለመደውን የተሳለጠ አገልግሎት ለመስጠት ተዘጋጅቷል ነው የተባለው።

ተጨማሪ በረራዎች ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ ያለምንም መንገደኛ መኾኑን ታሳቢ ያደረገ የዋጋ ማስተካከያ የሚደረግ መኾኑንም ጠቁሟል።

የዋጋ ማስተካከያው ወደ ከተሞቹ የሚደረጉትን መደበኛ በረራዎች የማይመለከት መኾኑም ነው የተገለጸው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበቤት ውስጥ ተደብቆ የነበረን አደንዛዥ ዕጽ መያዙን የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
Next articleበም/ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኀላፊና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ መልእክት፦