
አዲስ አበባ: ታኅሣሥ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ አሚኮ በአዲስ አበባ ያስገነባውን አዲስ ስቱዲዮ ጎብኝተዋል። ተቋሙ በየጊዜው ራሱን በማዘመን ተወዳዳሪ እና ተደራሽነቱን እያሰፋ መምጣቱን ዋና አፈ ጉባኤዋ ገልጸዋል።
አፈ ጉባኤዋ አሚኮ ባለፉት 30 ዓመታት በመጣበት ጉዞ የክልሉን ሕዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባሻገር ራሱን በቴክኖሎጂ እና በብቁ የሰው ኅይል በመገንባት ተደራሽነቱን እያሳደገ መጥቷል ብለዋል። እንደሀገር ለግጭት መንስኤ የኾኑ ነጠላ ትርክቶችን በማስቀረትም የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩን በማጠናከር አሚኮ የጋራ ገዥ ትርክትን ለመገንባት ሢሠራ መቆየቱን አፈ ጉባኤዋ አንስተዋል።
በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ተአማኒ መረጃን ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የሚተጋው አሚኮ አዲስ አበባ ያስገነባው አዲስ ስቱዲዮም ከሀገር ውስጥ አልፎ ዓለም አቀፍ ተደራሽነቱን እና ተወዳዳሪነቱን ከፍ ለማድረግ ዕድል የሚፈጥር መኾኑን ነው ያስገነዘቡት።
በቀጣይም ሚዲያው አሁን የጀመራቸውን ሥራዎች አጠናክሮ በማስቀጠል ሀገር ከገባችበት ችግር የምትወጣበትን አማራጭ የመፍትሄ ሀሳቦችን በማቅረብ፣ አብሮነትን የሚያጠናክሩ የጋራ እሴቶች እንዲዳብሩ፣ ፈጣን እና ተአማኒ መረጃን ለሕዝቡ ማድረስ ላይ ትኩረት አድርጎ ሊሠራ እንደሚገባም አፈጉባኤዋ ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፦ ቤተልሄም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!