
ደብረ ብርሃን: ታኅሣሥ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት በሰሜን ሸዋ ዞን አንጓለላ እና ጠራ ወረዳ እየተሠሩ ያሉ የመስኖ ልማት እንቅስቃሴዎችን ተመልክተዋል ። የአንጓለላ እና ጠራ ወረዳ መስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሙሉጌታ ፍቅር በወረዳው የመስኖ ምንጭ ማጎልበት እና ለትልልቅ የመስኖ ሥራ የሚኾን ጥናት መከናወኑን ገልጸዋል። በወረዳው በጨኪ ቀበሌ ለመጠጥ ውኃ ከተሠራ መለስተኛ ጥልቅ ጉድጓድ 485 ሄክታር መሬት በማልማት ከ9 መቶ በላይ የአካባቢው ማኅበረሰብን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም አንስተዋል።
የወረዳው አሥተዳዳሪ ደረሰ ደመመ የአካባቢው ማኅበረሰብ በባሕላዊ መንገድ የመስኖ ሥራን እያከናወኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል። ተጠቃሚነታቸውን ለማስፋት እገዛ እንዲደረግም ጠይቀዋል። የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ በትንሽ የውኃ አማራጭ እየተሠራ ያለውን ተግባር አድንቀዋል።
በአማራ ክልል የተጀመሩ የመስኖ ሥራዎችን ለማጠናከር እንደሚሠራ የጠቆሙት የአማራ ክልል ምክር ቤት የግብርና እና አካባቢ ጥበቃ ውኃ ሃብት ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ከፍያለው ሙላት መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች ለእንዲህ አይነቱ ሥራ እርብርብ ቢያደርጉ የግብርናውን ዘርፍ ለመደገፍ አይነተኛ አማራጭ እንደሚኾን አንስተዋል ።
በአማራ ክልል ምክር ቤት የሴቶች ሕጻናት እና ወጣቶች ማኅበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አበራሽ ታደሰ ከዚህ በበለጠ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ከተቻለ በአርሶ አደሮች ሕይወት ላይ ሰፊ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ገልጸዋል። “በዞኑ ያለው የመስኖ ሥራ እንቅስቃሴ ተስፍ ሰጭ መኾኑንም” የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ተናግረዋል።
ዘጋቢ: ስንታየሁ ኃይሉ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!