
አዲስ አበባ: ታኅሣሥ 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሙሉቀን ሰጥዬ የተለያዩ ሒደቶችን አልፎ ለፍፃሜ የበቃውን እና በቅርቡ የሚመረቀውን የአዲስ አበባ ስቱዲዮ ለመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች አስጎብኝተዋል። አሚኮ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከቴሌቪዥን ስርጭት በተጨማሪ አሚኮ አዲስ ኤፍኤም 103.5 ጣቢያን በመክፈት የክልሉን ሕዝብ እሴት እና ባህል በማስተዋወቅ ትልቅ ሚና እየተወጣ እንደሆነ ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ሁለንትናዊ እንቅስቃሴዎችን ለአዲስ አበባ እና አካባቢው ኅብረተሰብ በማሳወቅ 7ኛ የሬዲዮ ጣቢያው ተግባሩ ትልቅ ነው ብለዋል። አሚኮ ከአዲስ አበባ ስቱዲዮ በመነሳት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች እና ክልሎች በመንቀሳቀስ የዜና እና ፕሮግራሞች እንዲሁም የቀጥታ ስርጭቶችን ጭምር እየሠራ እንደሆነም አብራርተዋል።
ይህም የኢትዮጵያውያንን አብሮነት በማጠናከር ለጋራ ገዥ ትርክት ግንባታ ቅድሚያ ሰጥተን እየሠራን ለመሆኑ ማሳያ ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው የአዲስ አበባ ስቱዲዮ ለዚህ ሚናው ትልቅ ነው ብለዋል። በቴሌቪዥን ብቻ ሳይሆን በሬዲዮም ጭምር የጋራ ማንነት ግንባታን አሚኮ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል። አሚኮ ባሉት የኤፍ ኤም ማቀባበያ ጣቢያዎቹ እና የመካከለኛ ሞገድ ሬዲዮ ጣቢያ ጭምር በአብዛኛው እና በጎረቤት ክልሎች ተደራሽ በመሆን ይህንን ተግባሩን አጠናክሯል ነው ያሉት።
አሚኮ በአረብኛና በእንግሊዘኛ የውጭ ቋንቋዎች ጭምር ተደራሽ በመሆን የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ እና እውነት ለዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ ለማስረዳት የበኩልን እየተወጣ እንደሆነም አንስተዋል። አሚኮ ዛሬ ላይ 2 የቴሌቪዥን ጣቢያ እና 7 የሬዲዮ ማሰራጫ ጣቢያዎች በተለያዩ የዲጂታል ሚዲያ አማራጮች እና ነባሩን የበኩር ጋዜጣ ጨምሮ በተለያዩ ቋንቋዎች በማተም ትልቅ ተቋም መሆን ያቻለ ነው ብለዋል።
እንደተቋም አሚኮ ከዚህ እንዲደርስ የክልሉ መንግሥት ትልቅ አስተዋፅኦ አለው ሲሉም ዋና ሥራ አስፈፃሚው ምስጋና አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!