
ፍኖተ ሰላም: ታኅሣሥ 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በሀገሪቱ ለሚከሰቱ ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ ችግሮች አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት በግንባር ቀደምትነት የሚታወቅ ተቋም ነው። ከሰብዓዊ እርዳታ በተጨማሪም የጤና ተቋማትን በማጠናከር እና በመደገፍ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የምዕራብ ጎጃም ዞን ቅርንጫፍጽ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሸጋው ከፋለ ተቋሙ ከዚህ በፊት ለጤና ተቋማት የመድኃኒት እና የቁሳቁስ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል። አሁን ደግሞ ከዩኤንኦቻ ጋር በመተባበር ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ በዞኑ ለሚገኙ 8 ሆስፒታሎች እና ሦስት የጤና ጣቢያዎች የሕክምና መሳሪያዎች ድጋፍ አድርጓል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ከሰብዓዊ እርዳታ በተጨማሪ በዞኑ ለሚገኙ የጤና ተቋማት በተደጋጋሚ ድጋፍ ማድረጉን የገለጹት ደግሞ የምዕራብ ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ሽታሁን ጌታቸው ናቸው። አሁን የተደረገው የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ የጤና ተቋማትን አገልግሎት ለማሳለጥ እንደሚያስችል ተናግረዋል ።
በድጋፍ ርክክቡ ላይ የተገኙት የምዕራብ ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ አጉማስ አንተነህ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ላደረገው ድጋፍ ምሥጋና አቅርበዋል። በዞኑ ያሉ የጤና ተቋማት ችግሮችን ለመፍታት ከሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በጋራ እንደሚሠራም ተናግረዋል።
ለዚህም ዞኑ አስፈላጊውን ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያደርግ ነው የገለጹት። ድጋፉን የተረከቡት የጤና ተቋማት የሥራ ኀላፊዎችም ከዚህ በፊት በሕክምና መሳሪያዎች እጥረት ምክንያት ይደርስ የነበረውን እንግልት እንደሚቀርፍላቸው ተናግረዋል። ለድጋፉም ምሥጋናቸውን አቅርበዋል ድጋፉም አልትራሳውንድ፣ ሲቢሲ ማሽን፣ ማይክሮስኮፕ እና ሌሎች የሕክምና መሳሪያዎችን ያካተተ ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!