ለሽግግር ፍትሕ ስኬታማነት ሁሉም ሊረባረብ ይገባል።

20

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ለሕግ ባለሙያዎች፣ ለባለ ድርሻ አካላት እና ለሥራ ኀላፊዎች በሽግግር ፍትሕ ምንነት፣ አተገባበር፣ ለዘላቂ እርቅ እና ሰላም ባለው አበርክቶ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥቷል። በሥልጠናው የመወያያ ጽሑፍ ቀርቧል። በሀገራዊ የሰላም እጦት ችግሮች፣ መንስኤዎች፣ መፍትሔዎቻቸው እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሀሳብ ተነስቶ ውይይት ተደርጎበታል።

በኢትዮጵያ እርቅ ተደርጎ ሰላም ስለሚሰፍንበት እና የሽግግር ፍትሕ ስለሚተገበርበት አካሄድ እና አማራጮች ዓለም ዓቀፉ ተሞክሮን ምሳሌ በማንሳት ማብራሪያ ተሰጥቶበታል። ከተሳታፊዎች መካከል በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የሙስና ወንጀል የሥራ ሂደት ዐቃቢ ሕግ ፍቃዴ ምሥጋናው የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ እና የሀገራችን ያለፉ ታሪኮችንም ዳስሰንበታል ነው ያሉት። ችግሮችን በእርቅ፣ በካሣ፣ በምህረት፣ በሕግ ለመፍታት እና ችግሮች ደግመው እንዳይከሰቱ የሽግግር ፍትሕ ወሳኝነት አለው ብለዋል።

የሽግግር ፍትሕ ውጤታማ እንዲኾን እስከ ታችኛው ማኅበረሰብ ማድረስ እና መተማመን መፍጠር እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት። ሁሉን አሳታፊ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ነው ያነሱት። የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) ግጭት እና መፈናቀል የበዛበትን የሀገሪቱን ችግር ለማስተካከል ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ መተግበር መፍትሔ እንደሆነ ገልጸዋል።

የሽግግር ፍትሕ ውጤታማ እንዲኾን ኅብረተሰቡ በባለቤትነት መሳተፍ አለበት፤ ሀገር የጋራ ናትና የመንግሥት ተቋማትም ተባብረው ወደ ሰላም የሚያመጣውን እና የጋራ ውይይት እና ስምምነት እንዲደረስ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም የሽግግር ፍትሕ ከመደበኛው በተለየ መንገድ ከችግር የሚያወጣ አሠራርን በመተግበር የቆየ ቁርሾን በመቅረፍ እና ለዘላቂ ሰላም፣ መተማመን እና መተባበር የሚሠራበት ነው ብለዋል።

ለዚህም ፖሊሲ ወጥቷል ያሉት ቢሮ ኀላፊው ሕዝቡ እንዲያግዝ ግንዛቤ እየፈጠርን ነው ብለዋል። በቀጣይ የፌዴራሉ መንግሥት በሚያስቀምጣቸው አቅጣጫዎች እና ፕሮግራሞች እንመራለን ነው ያሉት። የክልሉ ሕዝብም ችግሮችን በመለየት እና በመፍትሔውም እንዲሳተፍ እንደሚያስተባብሩ ነው የገለጹት።

በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ላይ ለባሕላዊ ሽምግልና እና ዳኝነት ተቋማት እውቅና እና ሥልጠና በመስጠት በሽግግር ፍትሑ አበርክቶ እንዲኖራቸው እየተሠራ መኾኑንም ነው አቶ ብርሃኑ የገለጹት። የሽግግር ፍትሕ ሀገራዊ እና ክልላዊ አተገባበር አለው ያሉት አቶ ብርሃኑ ግጭት ለበዛበት ክልል ደግሞ የበለጠ ጠቃሚ ነውና ሕዝቡ፣ የመንግሥት ተቋማት እና ሚዲያ ለክልሉ መረጋጋት የሚሠራ ሁሉ ለዘላቂ ሰላም እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ አማረ ሰጤ “የሽግግር ፍትሕ በሀገራችን ያለ መግባባት ችግሮችን ለመፍታት እና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እንደ አማራጭ ከተያዙ መፍትሔዎች ውስጥ አንዱ ነው” ብለዋል የሽግግር ፍትሕ በአግባቡ እንዲተገበር እና ሕዝቡ እንዲጠቀም የክልሉ መንግሥት በትኩረት እንደሚሠራ አቶ አማረ ገልጸዋል።ባለፉት ጊዜያት የተፈጸሙ ግጭቶችን በፍትሕ አፈላላጊ የእርቅ ሥርዓት ለመፍታት እና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ዓይነተኛ መሣሪያ ነውም ብለዋል።

የሕግ የበላይነት ተፈጥሮ ወደ ልማት ለመግባት በጸደቀው ፖሊሲ አማካይነት ሕዝቡን በማሥተባበር እና በማሳተፍ እንሠራለን ነው ያሉት። የምክር ቤቱ አንዱ ሚና የሕዝብ ጥያቄ እንዲመለስ ማድረግ ነው፤ በሕግ የሚመለሱት እንዳሉ ኾነው ለእንዲህ ዓይነት የመፍትሔ አሠራሮችም ድጋፍ በማድረግ እና በመከታተል ችግሮች እንዲፈቱ እናደርጋለን ብለዋል።

“አሁን ሥልጠና ላይ ነን፤ ዝርዝር ፕላን አዘጋጅተንም ወደ ተግባር በመግባት የምንሠራ ይኾናል” ብለዋል ምክትል አፈ ጉባኤው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አሚኮ ለምንፈልገው የሰላም እና የዴሞክራሲ ግንባታ ትልቅ አስተዋፅኦ እያደረገ ያለ ሚዲያ ነው” የአሚኮ የቦርድ ሰብሳቢ ይርጋ ሲሳይ
Next articleየኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ለምዕራብ ጎጃም ዞን የጤና ተቋማት የሕክምና መሳሪያዎች ድጋፍ አደረገ።