
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በ2017/18 የምርት ዘመን 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለማሰራጨት ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መኾኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አጀበ ስንሻው ገልጸዋል። ምክትል ኀላፊው እንዳሉት አሁን ላይ ማዳበሪያ የማጓጓዝ ሥራ እየተሠራ ይገኛል። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 136 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ክልሉ ገብቷል።
ወደ ወደብ እየቀረበ የሚገኘውን ማዳበሪያ ወደ ክልሉ ለማጓጓዝ የመጋዝን እና የማጓጓዣ ዝግጅት ተደርጓልም ብለዋል። በ2016/17 የምርት ዘመን በክልሉ 7 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ መሠራጨቱ ይታወሳል። ለዚህም ከግብርና መዋቅሩ ባለፈ ከጸጥታ፣ ከፋይናንስ እና ሌሎች ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ መሥራት በመቻሉ ግብዓቱን በወቅቱ እንዲቀርብ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
ይህም ኾኖ ግን በሥርጭት ወቅት አልፎ አልፎ ችግሮች እንደነበሩ እንስተዋል። በተያዘው የምርት ዘመንም በማዳበሪያ አቅርቦት እና በሥርጭት ወቅት ሊከሰት የሚችልን ሕገ ወጥነት ለመከላከል ከተለያዩ ተቋማት ጋር እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ማኅበረሰቡም ማዳበሪያ በሚፈለገው መንገድ እንዲሰራጭ እንዲተባበርም ጠይቀዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!