
ደብረ ማርቆስ: 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን የ2016 በጀት ዓመት የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አፈፃፀም እና የ2017 በጀት ዓመት የእቅድ ትውውቅ መድረክ በደብረ ማርቆስ ከተማ ተካሂዷል። በምሥራቅ ጎጃም ዞን የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎት በ2005 ዓ.ም በሁለት ወረዳዎች ላይ ተጀምሮ ዛሬ ላይ በ20 ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች ተግባራዊ እየተደረገ ነው ።
በዞኑ በ2016 በጀት ዓመት 500 ሺህ የሚደረሱ የማኀበረሰብ ክፍሎችን የጤና መድኅን አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ ከ80 በመቶ በላይ ማሳካት እንደተቻለ የዞኑ ጤና መምሪያ ኅላፊ የሺዋስ አንዱዓለም ተናግረዋል። መምሪያ ኀላፊው በ2016 በጀት ዓመት በደብረ ኤልያስ እና ማቻከል ወረዳዎች በፀጥታ ችግር ምክንያት የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎትን መተግበር አለመቻሉንም ገልጸዋል።
በ2017 በጀት ዓመትም ከ143 ሺህ በላይ ለሚኾኑ የመክፈል አቅም ለሌላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች በድጎማ በጀት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱንም ኅላፊው ተናግረዋል። በግምገማ እና በንቅናቄ መድረኩ የተገኙት የምሥራቅ ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ ዋለ አባተ በክልሉ የተከሰተው የሰላም መደፍረስ በጤናው ዘርፍ ላይ ያሳደረው ጫና ከፍተኛ ቢኾንም ማኅበረሰቡን የጤና መድኅን አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን በማድረግ አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል ነው ያሉት።
ምክትል አሥተዳዳሪው የንቅናቄ መድረኩ ባለፈው ዓመት የነበሩ መልካም ክንውኖች በማጠናከር እና ችግሮችን በማረም ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የምናደርግበት ሊኾን ይገባልም ብለዋል። በመድረኩ አሚኮ ያነጋገራቸው የጎዛምን ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ሙሉሰው ቀሬ በባለፈው ዓመት በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት የጤና መድኅን አተገባበር ዝቅተኛ እንደነበር አስታውሰዋል።
ዋና አሥተዳዳሪው በአካባቢው የታየውን አንፃራዊ ሰላም በመጠቀም ዜጎች የጤና መድኅን አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲኾኑ በትኩረት እየሠራን ነው ብለዋል። የእነብሴ ሳር ምድር እና የአዋበል ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት ኀላፊዎችም በባለፈው በጀት ዓመት የተከሰተውን የሰላም መድፈረስ ተቋቁመው የወረዳቸውን ማኅበረሰብ የጤና መድኅን አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ ችለናል ብለዋል።
በምሥራቅ ጎጃም ዞን የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን አገልገሎት ከጥር 01/2017 ዓ.ም ጀምሮ የአባላት ምዝገባ እና እድሳት ሲጀመር 505 ሺህ 462 የሚኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች የአገልግሎት ተጠቃሚ እንደሚኾኑ ይጠበቃል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!6