
ባሕር ዳር: 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በግብርና ግብዓት ሥርጭት ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል። በውይይቱ በ2016/17 የምርት ዘመን በግብዓት ሥርጭት ሂደት ላይ የታዩ ችግሮች ተገምግመዋል።
በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የኾኑት የባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደር ዋለልኝ አንዳርጌ እንዳሉት በ2016/17 የምርት ዘመን በወቅቱ ግብዓት የቀረበበት እና በመጠንም የተሻለ እንደነበር ገልጸዋል። ይሁን እንጅ ቀድሞ መሰራጨት የሚገባው ግብዓት የመዘግየት ችግር እንደነበር ነው ያነሱት። ከ2017/18 የምርት ዘመንም የግብርና ግብዓቱ የተሻለ አቅርቦት እንዲኖረው እና በወቅቱም ወደ አርሶ አደሮች እንዲደርስ ጠይቀዋል።
የመርከብ ሁለገብ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየን ሥራ አሥኪያጅ ጌታቸው እሸቱ እንዳሉት ዩኒየኑ በ2016/17 የምርት ዘመን ከ1 ሚሊዮን 30 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለሰባት ወረዳዎች ተደራሽ አድርጓል። አሁን ላይ ለመስኖ ልማት 32 ሺህ 174 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ መሰራጨቱን ገልጸዋል። ዩኒየኑ ከማኅበረሰቡ ጋር በመቀናጀት የተመደበውን ግብዓት ሙሉ በሙሉ በማድረስ ኀላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
ዩኒየኑ በ2017/18 የምርት ዘመንም 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳቀሪያ በዞኑ ለማሰራጨት ቅድመ ዝግጅት አድርጓል። በይልማና ዴንሳ፣ ባሕር ዳር እና መርዓዊ ከተሞች ከሚገኙ ማዕከላት ወደ አርሶ አደሮች የሚሠራጭ ይኾናል። ለዚህ ደግሞ መሠረታዊ ኅብረት ሥራ ማኅበራት የመጋዝን ዝግጅት እና የሰው ኀይል ማሟላት ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ። ወረዳዎች የተደለደለላቸውን ግብዓት በፍትሐዊነት ለአርሶ አደሮች እንዲያሰራጩ ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።
የሰሜን ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ መልካሙ አለኸኝ እንዳሉት የ2017/18 የምርት ዘመን በዞኑ 286 ሺህ 211 ሄክታር መሬት በማልማት ከ13 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዷል። ይህንን ምርት ለማግኘት ከ1 ሚሊዮን 256 ሺህ በላይ ማዳበሪያ ለማሰራጨት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል። በወረዳዎች የመልማት አቅም መሠረት ደልድል መሠራቱን ነው የገለጹት።
በሥርጭት ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!