“ከጂቡቲ ፕሬዚዳንት ጋር ፍሬያማ ውይይት አድርገናል” ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ.ር)

11

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ.ር) ከጂቡቲ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌ እና ሌሎች የሥራ ኀላፊዎች ጋር በወደብ አጠቃቀም እና በሌሎች የሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በጅቡቲ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት ሚኒስትሩ ከጂቡቲ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ የጉብኝቱ ዓላማ በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር ለማድረግ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ እና ጂቡቲ በጣም ልዩ እና ጠንካራ ትብብር እንዳላቸውም ገልጸዋል።

ከጂቡቲ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌ እና ከውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ማሕሙድ አሊ የሱፍ ጋር በሁለትዮሽ እና በቀጣናዊ የፖለቲካ እና የደኅንነት ጉዳዮች ላይ በትብብር መሥራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መወያየታቸውን ገልጸዋል።

በንግድ ጉዳዮች፣ በወደብ አጠቃቀም እና በወቅታዊ ቀጣናዊ ደኅንነት ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውንም ለአብነት ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያና ጂቡቲ በባቡር፣ በወደብ እና በመሠረተ ልማት መስኮች ረጅም ዘመናትን የተሻገረ ታሪካዊ ወዳጅነት ያላቸው አገራት መኾናቸውንም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላይ ያለው መረጃ ያመለክታል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሕዝቡ ልጆቼ እንዳይማሩ የሚከለክል ሁሉ ጠላቴ ነው ሊል ይገባል” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)
Next articleግብዓት በወቅቱ ለማቅረብ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየሠራ መኾኑን የሰሜን ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ገለጸ።