
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የትምህርት ተቋማት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነዋል፡፡ ተማሪዎቹ ከትምህርት ገበታ ውጭ የኾኑ ለቀናት፣ ለሳምንታት እና ለወራት ብቻ አይደለም ለዓመታት ኾኗል እንጂ፡፡
በልጆቻቸው ተስፋ ያደረጉ ወላጆች የተስፋቸውን ፍሬ በዘመኑ እንዳይበሉ እንቅፋት ኾኗል፡፡ ነገን ለማሳመር ተስፋ የሰነቁ ልጆች ያለ በደላቸው ከዕድሜያቸው ላይ ተሠርቀዋል፡፡ ከእኩዮቻቸው ጋር እንዳይወዳደሩ ኾነዋል፡፡ ከትምህርት ርቀው በቁዘማ እንዲኖሩ ተገድደዋል፡፡ ሕጻናት የመማር መብታቸውን ተነፍገዋል፡፡ በትምህርት ቤቶቻቸው እንዳይንቀሳቀሱ ገደብ ተጥሎባቸዋል፡፡ መምህራን ሠርተው እንዳይኖሩ ተደርገዋል፡፡
እናስተምራለን ባሉ መገፋት ደርሶባቸዋል፡፡ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት የሚልኩ ወላጆች የግድያ ዛቻ ደርሶባቸዋል፡፡ ከአሚኮ ወቅታዊ ጋር ቆይታ ያደረጉት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) የመማር መብት መጣስ ከሕጻናት መብት ጥሰት ጋር ይያያዛል ነው የሚሉት፡፡
የነገዋን ኢትዮጵያን ለማሳመር የዛሬው ትውልድ ላይ መሥራት ግድ ይለናል፤ ዛሬ የሚገነባው ትውልድ የነገውን የኢትዮጵያ ገጽታ የሚያንጸባርቅ ነው ይላሉ፡፡ በአማራ ክልል የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሕጻናት ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ አድርጓል፡፡ በ2017 የትምህርት ዘመን ሰባት ሚሊዮን ተማሪዎችን እናስተምራለን ብለን አቅደን አፈጻጸማችን ዝቅተኛ ነው ይላሉ፡፡
ለትምህርት ዘመኑ ከወረሐ ነሐሴ/2016 ዓ.ም ጀምሮ ተማሪዎች እንዲመዘገቡ ጥረት ቢደረግም በሚፈለገው ልክ አልኾነም ነው የሚሉት፡፡ በጸጥታው ምክንያት ተማሪዎች ከትምህርት ርቀዋል፡፡ ትምህርት ቤቶችም ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ከትምህርት ገበታ ርቀው የቆዩ ተማሪዎች ወደ ትምህርት እንዲመጡ ጥረት እያደረግን ነው ብለዋል፡፡
በዘመናት መካከል፣ በተለያዩ ሀገራት እና ፖለቲከኞች የፖለቲካ ልዩነት ይኖራል የሚሉት ኀላፊዋ ትምህርትን ግን ለፖለቲካ መጠቀሚያ ማድረግ እና ትውልድን መጉዳት የተገባ አይደለም ነው የሚሉት፡፡ በግጭቱ ምክንያት ተማሪዎች እና መምህራን በሥነ ልቦና ተጎድተዋል ነው ያሉት፡፡ ዕድሜያቸው ባክኗልም ብለዋል፡፡
ልጆችን ከትምህርት ቤት ማስቀረት ሚሳኤል ከመወርወር ያልተናነሰ ጥቃት ነው፤ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ ሁሉም ሊያግዝ ይገባዋል ነው የሚሉት፡፡ እታገላለሁ የሚሉ አካላትም የሚታገሉት ለሕዝብ ከኾነ ሕጻናትን ያለ ሐጥያታቸው ጨለማ ውስጥ እንዲኖሩ መፍረድ የለባቸውም ነው ያሉት፡፡ በሕጻናት ሕይዎት ላይ መቀለድ የተገባ አይደለም ብለዋል፡፡
ሕጻናትን ከትምህርት ቤት አስቀርቶ መታገል ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የማይመጥን የትግል ስልት መኾኑንም አንስተዋል፡፡ የትምህርት ተቋማትን ከመዝጋት እና ተማሪዎች እንዳይማሩ ከማድረግ የበለጠ ጥፋት የለም ነው ያሉት፡፡ የትኛውም አካል ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዳይመለሱ የሚያደርገውን አካሄድ በቃህ ሊለው ይገባልም ብለዋል፡፡
“ሕዝቡ ልጆቼ እንዳይማሩ የሚከለክል ሁሉ ጠላቴ ነው ሊል ይገባል” ነው ያሉት፡፡ ሕዝቡ በትምህርት ጉዳይ የሚመጣበትን በቃህ ሊለው ይገባል፤ ትምህርት ቤቶችን መጠበቅም አለበት ብለዋል፡፡ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ እንሞታለን እንጂ ድጋሜ ልጆቻችን ከትምህርት ገበታ ውጭ አይኾኑም እያሉ መኾናቸውንም አንስተዋል፡፡ ሁሉም ኅብረተሰብ በዚህ ልክ በቃችሁ ሊል ይገባል ነው ያሉት፡፡
ተማሪዎችን እናስተምር ያሉ መምህራን ችግር እንደደረሰባቸውም አንስተዋል፡፡ መምህር ራሱን እንደሻማ እያበራ ለሌሎች ሕይዎት የሚኖር ነው ብለዋል፡፡ ኅብረተሰቡ መምህራንን መጠበቅ እንደሚገባውም አመላክተዋል፡፡ ያለፈው ዓመት ይበቃል ዘንድሮ ተማሪዎች ሳይማሩ እንዲከርሙ መፍቀድ አይገባም ነው ያሉት፡፡
በትምህርት ላይ የሚደርስ ጉዳት በትውልድ ላይ ክፍተት የሚፈጥር መኾኑንም አንስተዋል፡፡ የትምህርት ስብራት የትውልድ ሥብራትን ይፈጥራል፤ ሁሉም ሊያወግዘው ይገባል፤ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችም ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ የኾኑበትን መንገድ በቃ ሊሉ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ታጣቂ ኀይሎች መጠለያ ያደረጓቸው በርካታ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውንም አስታውቀዋል፡፡ የትኛውም አካል በቃችሁ ብሎ ሊነሳ ይገባል ብለዋል፡፡ የሰበዓዊ መብት ተሟጋቾች በለሆሳስ ከመጻፍ ባለፈ በአደባባይ ወጥተው ማውገዝ አለባቸው ነው ያሉት፡፡ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ የሚያደርገውን ጥረት ሁሉም ማገዝ እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡
ትምህርትን መደገፍ ትውልድን መደገፍ፣ የነገዋን ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ መሥራት መኾኑንም አመላክተዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!