ለሽግግር ፍትሕ ስኬታማነት ሁሉም አካል ድርሻ አለው” የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ

32

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ “የሽግግር ፍትሕ አሥተዳደር” በሚል መሪ ሃሳብ ለባለድርሻ አካላት የአቅም ግንባታ ሥልጠና እየሰጠ ነው። የሽግግር ፍትሕ ዓላማዎችን እና መርኾዎችን በመገንዘብ በኢትዮጵያ ሊደረግ ለታሰበው የሽግግር ፍትሕ ግንዛቤ የመፍጠር አካል በኾነው ሥልጠና የዞን እና የክልል የፍትሕ አካላት እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻዎች ተካፍለዋል።

የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም የሽግግር ፍትሕ ዓላማ ችግሮችን በመደበኛ ሕግ መፍታት በማይቻል ጊዜ የተበላሹትን በማቃናት፣ የተበደሉትን በማካካስ፣ እርቅ በመፍጠር እና በመፍታት ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ዓይነተኛ መፍትሄ መኾኑን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የተፈጠሩ ችግሮችን በሽግግር ፍትሕ እልባት እንዲያገኙ የሚያስችል አሠራር በማደራጀት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሰፊ ውይይት ሲደረግ ቆይቷል።

ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ጋር የተጣጣመ፣ ሰብዓዊ መብት ተኮር የኾነ እና የሀገሪቱን ነባራዊ ኹኔታ ግምት ውስጥ ያስገባ አሠራርን ለመተግበር የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ወጥቷል። በዚህም መሠረት ዕውነትን በማፈላለግ እና ዘላቂ መፍትሄ በማበጀት በኩል ክልሎች የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ ይጠበቃል ነው ያሉት።

ክልሎችም የተፈጠሩ ግጭቶች ቆመው፣ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን፣ ዕውነትን የማፈላለግ፣ የተፈናቀሉትን በመመለስ፣ በአጥፊዎች ላይ ተጠያቂነትን በማረጋገጥ ብሎም የተበደሉ አካላት እንዲካሱ በማድረግ ዘላቂ ሰላም እና መተማመን እንዲኖር ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ነው አቶ ብርሃኑ የተናገሩት።

የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ በክልሉ የሽግግር ፍትሕ እንዲጠናከር የሚያስችሉ ኹኔታዎችን በመፍጠር፣ ቅንጅታዊ አሠራርን በመከተል እና ስለ ሽግግር ፍትሕ ለሕዝቡ ግንዛቤ በመፍጠር የሽግግር ፍትሕ ውጤታማ እንዲኾን የመሥራት ኀላፊነት እንዳለበት አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል።

ኀላፊው ካለፈው በጀት ዓመት ጀምሮ ስለ ሽግግር ፍትሕ ምንነት፣ አስፈላጊነት እና ተያያዥ ጉዳዮች ለሕዝቡ እና ለባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል። ሥራውንም ከአጋር አካላት ጋር ለመሥራት በሽግግር ፍትሕ አስፈላጊነት እና ጠቀሜታ ላይ በመግባባት የግንዛቤ ፈጠራ እና የአቅም ግንባታ ሥራ መቀጠሉን ጠቅሰዋል።

“ለሽግግር ፍትሕ ስኬታማነት ሁሉም አካል ድርሻ አለው” ያሉት አቶ ብርሃኑ የውይይቱ ተሳታፊዎችም ለተግባሩ ውጤታማነት ያለባቸውን ኀላፊነት ተረድተው ለሽግግር ፍትሕ ተግባራዊነት ዕውቀት እና አቅም በመገንባት የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ብሔራዊ ቤተ-መንግስሥቱ የታሪካችን መድብል፣ የተጋድሏችን እና የድሎቻችን ድርሳን ነዉ” ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ
Next articleበውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ በዶራሌ ሁለገብ ወደብ ተገኝቶ የ2017/18 የአፈር ማዳበሪያ ኦፕሬሽን ውይይት አደረገ።