
አዲስ አበባ: ታኅሣሥ 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የብሔራዊ ቤተ መንግሥት ታደሶ ለዕይታ ክፍት ኾኗል። ቤተ-መንግሥቱ በብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና በተጋባዥ እንግዶች ተጎብኝቷል። በጉብኝቱ የተገኙት ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ “ቤተ-መንግሥቱ በእንዲህ እጹብ ድንቅ ኹኔታ ታድሶ በማየቴ ደስታዬ ጥልቅ ነዉ” ብለዋል።
ቤተ መንግሥቱ ከፍ ያለ ኪናዊ ጥበብ የተላበሰ ሕንፃ ብቻ አይደለም” የታሪካችን መድብል፣ የተጋድሏችን፣ የድሎቻችን እና የአያሌ ፈተናዎች፣ ዉጣ ዉረዶች የሚገለጽበት ድርሳን እንጅ” ብለዋል። ቤተ መንግሥቱ በሦሥት ምክንያት እንደተገነባ አስባለሁ፤ አንደኛ ዘመናዊነትን ለማስተዋወቅ ንጉሠ ነገሥቱ ከነበራቸው ጥልቅ ፍላጉጎት ጋር ይተሳሰራል።
ሁለተኛዉ የፋሽሸቱ ሞሶሎኒን ወረራ ካሸነፍንበት ጥቂት ዓመታት በኋላ መሆኾኑ ንጉሠ ነገሥቱ ሊያስተላልፉ የፈለጉት መልዕክት እንዳለ ያስገነዝባል። ሌላኛው ብርቱ ችግሮችን አሳልፈን ከመቼዉም በተሻለ ኹኔታ ጠንክረን ተመልሰናል እንደማለት ነዉም ብለዋል። አዲስ አበባ የነጻነት ብርሐን እንድትኾን የሚያደርግም ነው ብለዋል።
ቤተ-መንግሥቱ የዲፕሎማሲ እና የዉጭ ግንኙነት መስተጋብር የሚታይበት ነዉ። ቦታዉ ከንጉሠ ነገሥታዊ ደማቅ ስብሰባዎች እስከ ዉስብስብ የዲፕሎማሲ ድርድሮች እንደተካሄዱበት ዛሬም አሻራዉ እንደሚታይም ፕሬዚዳንቱ አስገንዝበዋል። ቤተ መንግሥቱ የኢትዮጵያን እና የአፍሪካን ዲፕሎማሲ ዉጣ ዉረድ እና ፍሰት አስተናግዷል ነው ያሉት።
የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ ወይንም የመጀመሪያው የአፍሪካውያን አሕጉራዊ ድርጅት እንዲመሠረት የተደረገዉ በዚህ ቤተ መንግሥት በተደረገዉ የዉይይት ዉጤት እንደኾነም አስታዉሰዋል። ፕሬዚዳንቱ የቤተ-መንግሥቱን ፋይዳ እና ቀጣይነት ላከበሩት ሠራተኞች ልዩ አድናቆት እና ምስጋና አቅርበዋል።
ታሪክን ማወቅ፣ መጠበቅ እና ማስቀጠል ትዉልዳዊ አደራ እና ኀላፊነት መኾኑን መገንዘብ እና ከዚህ ቤተ መንግሥትም መማር ይገባል ብለዋል።
ዘጋበ: በለጠ ታረቀኝ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!