“ብዝኀ የማዕድን ሀብት ፍለጋ እና የማምረት ሂደት ትኩረት እየተሰጠው ነው” ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ

41

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) መንግሥት ተረስቶ የቆየውን የማዕድን ጸጋ በመግለጽ የሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ምሰሶ እንዲሆን ማድረጉን የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እና የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ ገልጸዋል። ሚኒስትሩ በብልጽግና ፓርቲ አንደኛ ጉባዔ የብዝኃ ዘርፍ ኢኮኖሚ የዕድገት ምንጭ የሆነውን የማዕድን ጸጋ መግለጽ እንደሚገባ አቅጣጫ መቀመጡን አውስተዋል።

ኢትዮጵያ በርካታ የማዕድን ጸጋ ያላት ሀገር መኾኗን ተናግረዋል። ከለውጡ ዓመታት በፊት ዘርፉ በመንግሥት ዘንድ የተረሳ እና ለሕገ ወጥነት የተጋለጠ ነበር ብለዋል። ለውጡን ተከትሎ ባለፉት ስድስት ዓመታት ከፖሊሲ እና ሕግጋት ጀምሮ የዕይታ ለውጥ በማድረግ የሀገርን የማዕድን ጸጋ የማወቅ እና የመግለጽ ሰፊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል።

በ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድም ዘርፉን ከአምስቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ምሰሶዎች አንዱ በማድረግ ትኩረት መስጠቱን አስረድተዋል። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ደግሞ በወርቅ እና በሌሎች ማዕድናት የወጪ ንግድ ላይ ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱን አንስተዋል። ለአብነትም በወርቅ የወጪ ንግድ ብቻ ለዓመታት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ባለፉት ስድስት ወራት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ መገኘቱን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል መንግሥት የሲሚንቶ ዋጋ እና የምርት እጥረት ላይ ሕዝቡ የሚያነሳውን ቅሬታ ለመፍታት እርምጃ መውሰዱን በማንሳት፣ የግሉን ዘርፍ በማንቀሳቀስ እና ግዙፍ ፋብሪካዎች በመክፈት እልባት መስጠቱን ተናግረዋል። በዚህም አሁን ላይ የግንባታ ኢንዱስትሪው ሲሚንቶ በቀላሉ የሚገኝበት ሁኔታ መፈጠሩን ነው ያነሱት።

በወርቅ ምርት ላይ ብቻ የነበረውን ትኩረት በማስፋት “ብዝሃ የማዕድን ሀብት ፍለጋ እና የማምረት ሂደትም ትኩረት እየተሰጠው ነው” ብለዋል። በዘርፉ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የመተካት ሥራውም በተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ነው ብለዋል። የሀገር ዕድገት ከማዕድን ጋር ከፍተኛ ቁርኝት እንዳለው ያነሱት ሚኒስትሩ፥ ማዕድን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለሚደረገው መዋቅራዊ ሽግግር ዋነኛ መሳሪያ መሆኑን ተናግረዋል።

ዘርፉ ለሕገ ወጥነት ተጋላጭ በመኾኑ መንግሥት ብሔራዊ ምክር ቤት አቋቁሞ እርምጃ እየወሰደ ሲሆን፥ ሌሎች ችግሮችን ለመፍታትም ተቋማት በቅንጅት እየሠሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። ማዕድን ለወጣቶች የሥራ ዕድል የሚፈጠርበት እና የዜጎች ሕይወት የሚቀየርበት እንዲሆን በማድረግ በኩልም ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ መኾኑንም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላይ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር በ100 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
Next articleየአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ በኢትዮጵያ ሊደረግ ለታሰበው የሽግግር ፍትሕ ግንዛቤ ለመፍጠር እየሠራ ነው።