የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር በ100 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

24

ባሕር ዳር: ታኅሳስ 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ)በበጎ አድራጎት ሥራቸው በዓለም ዙሪያ ዝናን ያተረፉት 39ኛው የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር በ100 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2022 የዓለም የሰላም ኖቤል ተሸላሚው እና በአሜሪካ ታሪክ እረጅሙን ዕድሜ በሕይዎት የኖሩት የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር በጆርጂያ ግዛት በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በወዳጅ ዘመዶቻቸው ተከበው በሰላም ማረፋቸውን በስማቸው ያቋቋሙት የእርዳታ ድርጅት “የካርተር ማእከል” በድረገጹ አስታውቋል።

የጂሚ ካርተርን ሕልፈት ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እና ከቀናት በኋላ ነጩ ቤተመንግሥት ይደርሳሉ ተብለው የሚጠበቁት አዲሱ ተመራጭ ፕሬዚዳንት ዶናንድ ትራምፕን ጨምሮ የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ሀዘናቸውን እየገለፁ ይገኛሉ። የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮንም በጂሚ ካርተር ሕልፈት የተሰማቸውን ሀዘን በኤክስ ገጻቸው ገልፀዋል።

ጂሚ ካርተር 1982 በስማቸው ያቋቋሙት የእርዳታ ድርጅት “የካርተር ማዕከል” ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለም ከ80 በላይ ሀገራት ላይ በምግብ ዋስትና ማረጋገጥ፣ በሰላም እና በጤና ጉዳዮች ላይ አተኩሮ የሚንቀሳቀስ የእርዳታ ድርጅት ነው። 1924 የተወለዱት ጂሚ ካርተር 4 ልጆች፣ 11 የልጅ ልጆች እና 14 የልጅ ልጅ ልጆችን ለማየት ታድለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየተማሪዎችን መጻሕፍት በእሳት ማቃጠል ለምን አስፈለገ፤ ትርጉሙስ ምንድን ነው?
Next article“ብዝኀ የማዕድን ሀብት ፍለጋ እና የማምረት ሂደት ትኩረት እየተሰጠው ነው” ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ