የተማሪዎችን መጻሕፍት በእሳት ማቃጠል ለምን አስፈለገ፤ ትርጉሙስ ምንድን ነው?

93

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ትውልድ የሚወጣበትን፣ የሀገር መጻዒ እድል የሚወሰንበትን፣ እውቀት የሚገበይበትን መጽሐፍ ማቃጠል ለምን አስፈለገ? ለሕዝብ መቆርቆር ሃብቱን እና ንብረቱን ማጥፋት፣ የልጆቹን ተስፋስ መቀማት ነውን?

በደቡብ ጎንደር ዞን እብናት ወረዳ የተማሪዎቹ መጽሐፍ ተቃጥሏል፡፡ ዕውቀትን የተራቡ ልጆች ይጠብቁት የነበረው መማሪያ መጽሐፍ በታጠቁ ኀይሎች ወደ አመድነት ተቀይሯል፡፡ ለሕዝብ እናስባላን ማለት ከትምህርት ጋር አለያይቶ ማኖር ይኾንን?

እነዚህ ኀይሎች ከዚህ በፊትም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ ሲከለክሉ ከርመዋል፡፡ የጥፋት በትራቸውን በተማሪዎች ላይ አሳርፈዋል፡፡ እያሳረፉም ነው፡፡ ተማሪዎች ለምን እንዲማሩ አልተፈለገም? ስለምንስ እንዲያውቁ እንዲጠይቁ እና እንዲያንሰላስሉ አልወደዱም? የተፈለገው ትውልድ እንዳይቀጥል ይኾንን?

ይህ ከክፉ ዓላማ የሚነጭ ነው፡፡ ይህ የሚኾነው ደግሞ ታቀዶበት እና ታስቦበት ይመስላል፡፡ እኩይ ተግባሩ የሚመዘዘው ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ ሀገር ነው፡፡ የወላጆቻቸው ተስፋ ይኾናሉ ነገ ሀገር ያሻግራሉ የተባሉ ልጆች እንዳይማሩ እየተደረጉ፤ እንዳያውቁ እና እንዳይጠይቁ እየተከለከሉ ነውና፡፡ ነገ ሀገር የሚረከቡት እና ተወዳዳሪ ለመኾን የሚያልሙት ያለ በደላቸው ከእድሜያቸው ላይ እየተሰረቁ ነው፡፡

የታጣቂ ኀይሎች ሕልም እና ዓላማ ምን እንደኾነ በደቡብ ጎንደር ዞን እብናት ወረዳ ታይቷል፡፡ በተግባርም ተገልጧል፡፡ ለወትሮው በአፋቸው እንወድሃለን፣ እንታገልልሀለን የሚሉት ኃይሎች ምግባራቸው ግን ከዚህ በተቃራኒ ያለውን እውነት አሳይቶታል፡፡

የእብናት ወረዳ ተማሪዎች መማሪያ መጽሐፍ የሚሹ እና አንድ መጽሐፍ እስከ አምስት ተማሪ ድረስ እየተዋዋሱ ነገን ብሩህ ለማድረግ የሚታትሩ እንደኾነ ተነግሯል፡፡ የእነዚህን ተማሪዎች የነገ ተስፋ ለማፍካት እና እውን ለማድረግ ቀለም የሚቆጥሩበት፣ ለነገ መሻገሪያ ምርኩዝ የሚኾናቸው መጻሕፍትን ለማድረስ በመንግሥት በኩል ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ መጽሐፍትን ለማሳተምም ብዙ ንዋይ ፈሰስ ተደርጓል፡፡ ወላጆችም ልጆቻቸው ይማሩላቸው ዘንድ ለመጻሕፍት ማሳተሚያ መቀነታቸውን ፈትተው ካላቸው ሰጥተዋል፡፡

የእብናት ወረዳ አሥተዳደሪ ቻላቸው መሳፍንት የተማሪዎችን የመጻሕፍት እጥረት ለመቅረፍ መጻሕፍትን የያዘ ተሸከርካሪ ወደ ወረዳው ሲጓዝ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ተሸከርካሪው ከዞኑ ዋና ከተማ ደብረ ታቦር ወደ እብናት በማቅናት ላይ እያለ ጥቃት እንደደረሰበት ነው የተናገሩት፡፡

ለሕዝብ እንቆረቆራለን የሚሉ ነገር ግን ተግባራቸው የሚሉትን የማያሳይ ጽንፈኞች ተሸከርካሪውን መንገድ ላይ ማስቆማቸውን የተናገሩት ዋና አሥተዳደሪው ፍላጎታቸው ትውልድ ማምከን ነውና እብናት ሊገባ 14 ኪሎ ሜትር ሲቀረው ያስቆሙትን ገልባጭ ተሽከርካሪ መጽሕፍቱን እንዲገለብጥ በማድረግ ማቃጠላቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ድርጊታቸውን ትወልዱን እንዴት እንደሚጠሉት በተግባር የገለጹበት መኾኑን ገልጸዋል፡፡

መረጃው የደረሰው የእብናት ወረዳ የጸጥታ ኀይል መጽሐፍቱን ለማዳን በስፍራው ቢደርስም ከቃጠሎ ማትረፍ አለመቻሉንም አንስተዋል፡፡ የተቃጠሉት መጻሕፍት ከ1ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ለሚማሩ ልጆች የታሰቡ እና ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ እንደወጣባቸው ተናግረዋል፡፡

ትምህርት ቤቶችን ሲዘጋ፣ የተማሪዎችን የመማር ፍላጎት ሲገታ እና ጊዜያቸውን ሲያባክን የቆየው ኀይል አሁን ደግሞ መጻሕፍትን በማቃጠል እኩይ ተግባሩን መግለጹን ነው ያመላከቱት፡፡ በተፈጠረው ክስተት የወረዳው ሕዝብ እና የመንግሥት አሥዳደር ማዘኑንም ገልጸዋል፡፡ የተፈጸመው ተግባር ከስብዕና የወረደ እና ለትውልዱ የማይመጥን በመኾኑ ሁሉም ዜጋ ድርጊቱን ሊያወግዘው እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጥምቀት በዓል በጎንደር በሰላም እንዲከበር ማድርግ የሁሉም ኀላፊነት መኾኑ ተገለጸ።
Next articleየቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር በ100 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።