
ጎንደር : ታኅሣሥ 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጥምቀት በዓል በጎንደር ሲከበር ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይኾኑ ዓለም አቀፍ እንግዶች የሚታደሙበት በዓል ነው። በዓሉን ሰላማዊ በኾነ መንገድ ለማክበር የሚያስችል ምክክር በጎንደር ከተማ ተካሂዷል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው የከተማዋን ሰላም ለማስከበር የሰላም ዘብ አባላቱ ከማኅበረሰቡ ጋር በመኾን በጋራ ሊሠሩ እንደሚገባ ተናግረዋል። የጥምቀት በዓል በመናገሻዋ ጎንደር በሰላም እንዲከበር ማድርግ የሁሉም ኀላፊነት ነው ብለዋል።
ሰላም ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መኾኑን ያነሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው መተጋገዝ እና ጎንደርን ወደ ፊት ማሻገር የመሪዎች ኀላፊነት ብቻ አለመኾኑን ጠቅሰዋል። ጎንደርን ለመለወጥ እኔም ኀላፊነት አለብኝ የሚል ማኅበረሰብ ሊፈጠር ይገባል ብለዋል።
የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ በሪሁን መንግሥቱ የጥምቀት በዓል በድምቀት እንዲከበር ለማድረግ የጸጥታ መዋቅሩ ተገቢ የኾነ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል።
ቀደም ባሉት ጊዜያትም ቢኾን ጎንደር ላይ ወጣቶች የጥምቀትን በዓል በማክበር በኩል ጥሩ ታሪክ አላቸዉ ያሉት ምክትል ኃላፊው በዚህ ዓመትም በተደራጀ መንገድ በዓሉ በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን አንስተዋል።
ከሀይማኖት አባቶች፣ ከማኅበረሰቡ እና ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር የቅንጅት ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
የጥምቀት በዓል ካሁን ቀደምም ሲከበር ሰላሙ የተጠበቀ እንዲኾን በማድረግ በኩል የተለያዩ ሥራዎች ሢሠሩ እንደነበር ያነሱት የመድረኩ ተሳታፊዎች በዓሉ የጎንደር መለያ እና የጋራ በዓላችን በመኾኑ በድምቀት እና በሰላም እንዲከበር እንሠራለን ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!