“ከጥር ወር ጀምሮ የማኅበረሰብ ዓቀፍ የጤና መድኅን አገልግሎት ምዝገባ ይጀመራል” የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ

32

ደብረ ማርቆስ: ታኅሣሥ 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ የ2016 ዓ.ም ዕቅድ አፈጻጸም እና የ2017 ዓ.ም የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።

”እንደ አቅሜ አዋጣለሁ እንደ ህመሜ እታከማለሁ” በሚል መሪ መልዕክት ነው የአፈጻጸም እና የንቅናቄ መድረክ የተካሄደው።

በ2016 ዓ.ም የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎት ማኀበረሰቡን በጥራት እና በፍትሃዊነት ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት የተሠራበት እንደ ነበር የከተማ አሥተዳደሩ ጤና መምሪያ ኀላፊ ሀብቴ ወርቁ አስታውሰዋል።

በ2017 ዓ.ም የመክፈል ዓቅምን መሠረት ያደረገ የጤና መድኅን አገልግሎት ተግባራዊ እንደሚደረግ ነው የገለጹት ኀላፊው። በአልግሎት አሰጣጡ በኩል የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚተገበርም ተናግረዋል።

በንቅናቄ መድረኩ የተገኙት የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ ከአገልግሎት አሰጣጡ አንጻር የተስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በተለይም ከመድኃኒት አቅርቦት ጋር የሚነሳውን ችግር ለመቅረፍ ከተማ አሥተዳደሩ ለማኅበረሰቡ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ መድኃኒት ቤቶችን ለመክፈት ዓቅዶ እየተሠራ ነው ብለዋል።

በ2016 ዓ.ም በሰላም እጦት ውስጥ ኾነን የማኅበረሰብ ዓቀፍ ጤና መድኅን አባላትን በማፍራት በኩል ጥሩ አፈጻጸም ነበረን ያሉት የመድረኩ ተሳታፊዎች በ2017 በጀት ዓመት የተሻለ ተግባር ለማስመዝገብ በቅንጅት እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

በከተማ አሥተዳደሩ በ2017 በጀት ዓመት “የጤና መድኅን አገልግሎት ከጥር ወር ጀምሮ ምዝገባ የሚጀምር ሲኾን” ከ30 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሠራም ተገልጿል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተደራራቢ ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦችን በዕድሜ ልክ ጽኑ እሥራት ቀጣ።
Next articleየጥምቀት በዓል በጎንደር በሰላም እንዲከበር ማድርግ የሁሉም ኀላፊነት መኾኑ ተገለጸ።