
ሁመራ፡ ታኅሳስ 19/04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በቀን 14/04/2017 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተክላይ ፀጋይ የተባለን ወጣት በማገት፤ ከቤተሰቡ ገንዘብ በመቀበል እና ግድያ በፈፀሙ ሁለት ወንጀለኞች ላይ በእያንዳንዳቸው የዕድሜ ልክ እና በአንድ ወንጀለኛ ላይ ደግሞ የ10 ዓመት ብይን መስጠቱን ፍርድ ቤቱ ገልጿል።
የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዐቃቢ ሕግ እና የመደበኛ ወንጀሎች የሥራ ሂደት አሰተባባሪ ታዬ ብርሃኑ የግድያ ወንጀሉ የተፈፀመው በቃፍታ ሁመራ ወረዳ ልጉዲ በተባለ አካባቢ እንደኾነ ገልጸዋል።
1ኛ እና 2ኛ ተከሳሽ የግል ተበዳዩን ከገደሉ በኋላ 1ኛ ተከሳሽ በሟቹ ስልክ ወደ ቤተሰቦቹ በመደወል ገንዘብ ከላኩለት ልጃቸውን በሕይዎት እንደሚለቁ በመናገር ከቤተሰቡ 40 ሺህ ብር ተቀብሏል ብለዋል።
የተፈፀመውን የወንጀል አስከፊነት በመረዳት የዞኑ ዓቃቢ ሕግ መምሪያ፣ የዞኑ ፖሊስ መምሪያ እና የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመበት ወረዳ ፖሊስ መርማሪዎች የተካተቱበት የምርመራ ቡድን በማደራጀት የሰው፣ የቴክኒክ እና የፎረንሲክ ማስረጃ በማሠባሠብ የወንጀል ድርጊቱ ስለመፈፀሙ እንዲረጋገጥ ብሎም ወንጀል ፈፃሚዎችም ድርጊቱን ስለመፈፀማቸው ቃላቸውን እንዲሰጡ መደረጉን ዐቃቢ ሕጉ አስረድተዋል።
የሰነድ እና የሰው ማስረጃዎች ከተጠናከሩ በኋላ ዓቃቢ ሕግ የተፈፀመው ወንጀል ይመጥናል ያለውን ክስ በሦስቱም ተከሳሾች ላይ የመሠረተ ሲኾን የመጀመሪያው ክስ ሦስቱም ተከሳሾች በከባድ የእገታ ወንጀል፣ በግድያ ወንጀል እና በማታለል ወንጀል ክስ በመመሥረት ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማቅረቡን ተናግረዋል።
ፍርድ ቤቶች የሚጠበቅባቸውን ነፃነት እና ገለልተኝነት በጉልህ ያሳዩበት የፍርድ ሂደት መኾኑን የጠቆሙት ዐቃቢ ሕጉ ፍርድ ቤቶች እና “ማንኛውም ማኅበረሰብ የሕግ እና የሥርዓት የመጨረሻ ማስከበሪያ አድርጎ የሚጠቀምባቸው” መሳሪያዎቹ መኾናቸውን በመግለጽ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድቤትም ይሄንኑ ተግባር እንዳረጋገጠ ገልጸዋል።
ማንኛውም ሰው ወንጀል ፈጽሞ በመሰወር ከቅጣት ማምለጥ እንደማይቻል የተረጋጠበት እና ማንኛውም ግለሰብ ከወንጀል ድርጊት መታቀብ እንደሚገባው አስተማሪ ፍርድ እንደኾነ አስረድተዋል።
ሰላም እና ደኅንነት በጸጥታ መዋቅር ብቻ አይረጋገጥም ያሉት ደግሞ የዞኑ የሰላም እና ጸጥታ መረጀ አስተባባሪ ሻምበል እሸቴ አወቀ ናቸው።
በዚህ ድርጊት ላይ የተሳተፉ ወንጀለኞችን ለፍርድ በማቅረቡ ሂደት ላይ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ እንደነበር ተናግረዋል።
አቶ ሻምበል እሸቴ “የዞናችን ሕዝብ ሰላም ፈላጊ ነው፤ የተለያዩ ሕገወጥ ተግባራት ሁከት እንደሚያስከትሉ የሚገባው ሕዝብ ስለኾነ ሰላም እና ደኅንነትን ለማረጋገጥ ኅብረተሰቡ ግንባር ቀደም ነው” ብለዋል።
ሕዝቡ ለወንጀል እና ወንጀለኞች መደበቂያ መኾን እንደማይፈልግ የተናገሩት አቶ ሻምበል እሸቴ ወንጀል የሠራን ሰው ሳያጋልጡ መተው ራሱን መልሶ እንደሚጎዳው ሕዝቡ ግንዛቤ ማዳበሩን ገልጸዋል።
በመኾኑም ይሄንን ወንጀል ለማጋለጥ የሕዝቡ በተለይም የወጣቱ ተሳትፎ ከፍተኛ እንደነበር ተናግረዋል።
የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የፀረ ሙስና መርማሪ ዋና ክፍል ኀላፊ እና የወንጀል ታክቲክ መርማሪ ባለሙያ ምክትል ኢንስፔክተር ምሕረት አብ ብርሃኑ ወንጀለኞችን ለመያዝ ሳይንሳዊ እና ጥበብ የተሞላባቸውን ስልቶች መጠቀማቸውን ጠቅሰዋል።
ምክትል ኢንስፔክተሩ እንዲህ አይነት ወንጀሎች ከመፈፀማቸው በፊት በኅብረተሰቡ እና በጸጥታ አካላት ቅንጅት መከላከል እንደሚገባ ገልጸዋል። ትምህርት በመስጠት “ወንጀል ጠል ማኀበረሰብ መፍጠር ይገባልም” ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!