ከ2 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለማልማት ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

30

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አርሶ አደር ወልዴ መጠነ በምዕራብ ጎንደር ዞን ምዕራብ አርማጭሆ አብርሃ ጅራ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡

አርሶ አደሩ በ10 ሄክታር መሬት ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ በቆሎ እና ቃሪያ በመስኖ ልማት እያለሙ እንደኾነ ነግረውናል፡፡

ካለሙት ምርት በሄክታር ከ350 እስከ 450 ኩንታል ሊያገኙ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

መምሪያው አስፈላጊ ግብዓቶችን ማሟላቱን የተናገሩት አርሶ አደሩ ጀነሬተር በመጠቀም እያለሙ እንደኾነ ነው የሚገልጹት፡፡

የምዕራብ ጎንደር ዞን ከ242 ሺህ 963 ሄክታር መሬት በላይ በመስኖ ሊለማ የሚችል ከፍተኛ የኾነ የማምረት አቅም ያለው ዞን ነው፡፡

በበጀት ዓመቱ 2 ሺህ 652 ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ዕቅድ በመያዝ ወደ ሥራ መገባቱን የምዕራብ ጎንደር ዞን የመስኖ አትክልት እና ፍራፍሬ ቡድን መሪ አዲስዓለም ቢተው ተናግረዋል፡፡

ይህ ዜና አስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 2 ሺህ 159 ሄክታር መሬት በመስኖ ማልማት ተችሏል ነው ያሉት። ይህም የዕቅዱ 88 በመቶ የሚሸፍን ነው፡፡

በዚህ ዓመት ከሚመረተው የመሥኖ ልማት 494 ሺህ 433 ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅም ነው ያብራሩት።

የመስኖ ልማቱን ውጤታማ ለማድረግ 1ሺህ 656 የውኃ መሳቢያ ሞተሮችን እና የማዳበሪያ ግብዓቶችን ዞኑ ለአርሶ አደሮች ማድረሱንም አስገንዝበዋል።

መሪዎችን ጨምሮ እስከ ታች ያሉ የግብርና ባለሙያዎች እስከ ቀበሌ ድረስ በመውረድ ሥራው ውጤታማ እንዲኾን አስፈላጊውን የድጋፍ እና ክትትል ሥራ እየተሠራ ስለመኾኑም ጠቁመዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የተማሪዎች መማሪያ ቁሳቁስ እና መጻሕፍት በጽንፈኞች ተቃጠለ።
Next articleየወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተደራራቢ ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦችን በዕድሜ ልክ ጽኑ እሥራት ቀጣ።