ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የተማሪዎች መማሪያ ቁሳቁስ እና መጻሕፍት በጽንፈኞች ተቃጠለ።

62

ባሕር ዳር: ታኅሳስ 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ጎንደር አስተዳደር ዞን በእብናት ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የተማሪዎች መማሪያ ቁሳቁስ እና መጻሕፍት በጽንፈኞች ተቃጥሏል።

የእብናት ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ግዛቸው በላይ እንደገለጹት የትምህርት ስብራትን ለመጠገን በሀገር አቀፍ ደረጃ የትምህርት ፖሊሲ ለውጥ ተደርጎ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ነው። ከሚሠሩት ሥራዎች መካከል አንዱ እና ዋናው ደግሞ መማሪያ እና ማስተማሪያ መጻሕፍትን በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ማዘጋጀት ነበር ብለዋል።

ከዚህ ቀደም መጻሕፍቱን ወደ ወረዳው በበርካታ ጥረቶች በማስመጣት አዲሱን የትምህርት ፖሊሲ ከተገበርን ሁለት ዓመታትን አስቆጥረናል ያሉት ኀላፊው ነገር ግን ወደ ወረዳችን የመጡት የተማሪዎች መጽሐፍት በተማሪዎች ቁጥር ልክ አልነበሩም ነው ያሉ። የመጽሐፍ እጥረቱን ለመቅረፍ ታህሣሥ17/2017 ዓ.ም ከደብረ ታቦር ወደ እብናት ወረዳ የሚጓጓዝ የተማሪዎች መማሪያ መጽሐፍ በጽንፈኞች ተይዞ መቃጠሉን ገልጸዋል።

ትናንት ራሱን የአማራ ሕዝብ ነጻ አውጭ ነኝ ሲል የነበረው ጽንፈኛ ቡድን የትምህርት ተቋማትን ዘርፏል፤ የትምህርት ሥራ እንዲስተጓጎልም አድርጓል ብለዋል። ከልክ ያለፈውን የጽንፈኝነት መገለጫውን ደግሞ የተማሪዎችን መማሪያ መጻሕፍት በማቃጠል አሳይቶናል ብለዋል።

ኀላፊው አያይዘውም የትምህርት ተቋማት ከማንኛውም የፖለቲካ ተጽዕኖ ነጻ ኾነው እያለ እንደዚህ ዓይነት የውጭ ጠላት እንኳን የማይፈጽመው አስነዋሪ ተግባር መፈጸሙ በማኅበረሰቡ ሊወገዝ እንደሚገባ ጠቁመዋል። የወደሙ ተቋማት ሥራ እንዲጀምሩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉልም ጥሪ አቅርበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አዳዲስ ጉዳዮችን ለማካተት እንደ ክልል የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ አስፈልጓል”ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር)
Next articleከ2 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለማልማት ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡