“አዳዲስ ጉዳዮችን ለማካተት እንደ ክልል የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ አስፈልጓል”ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር)

74

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የሕግ፣ ፍትሕ እና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር ) የአማራ ክልል የጥብቅ ፍቃድ አሰጣጥ እና አሥተዳደርን በተመለከተ ውይይት እንደተደረገ ገልጸዋል። በሀገር አቀፍ ደረጃ አዋጅ 1249/2013 ጸድቆ ሥራ ላይ ቆይቷል ያሉት ዶክተር ደሴ ለውጡ የሚፈልጋቸውን አዳዲስ ጉዳዮች ለማካተት እንደ ክልል የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ አስፈልጓል ብለዋል።

ለጠበቆች እንዴት ፍቃድ እንደሚሰጥ በተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ ተካቷል፤ እስካሁን በኢትዮጵያ ታሪክ የጠበቆች ድርጅት አልነበረም፤ በረቂቅ አዋጁ ግን ሁለት እና ከዚህ በላይ የጥብቅና ፍቃድ ያላቸው የሕግ ሰዎች ኀላፊነቱ የተወሰነ የሽርክና ማኅበር እንዲያቋቁሙ ይፈቅዳል፤ ይህም ሙያው ይበልጥ እንዲዳብር የሚያስችል አዲስ አተያይ ነው ብለዋል።

በሕግ ትምህርት ቤት ሕግን የሚያስተምሩ ከዚህ በፊት ሕግ በሚፈቅደው መሠረት የጥብቅና ፍቃድ እንዲያወጡ የሚፈቅድ ሕግ አልነበረም፤ በ2013 ግን የሕግ መምህራን የጥብቅና አገልግሎት እንዲሰጡ በሀገር አቀፍ ደረጃ በአዲስ ተካትቷል፤ በሌሎች ሀገራትም ይሠራበታል፤ ይህም በክልል ደረጃ ዕውቅና እንዲሰጥ የሚፈቅድ ነው።

የሕግ መምህራን ፍቃዱን እግኝተው ጥብቅና ቢቆሙ አንድም በጥብቅና ክርክር ወቅት ከሚያገኙት ተሞክሮ ተማሪዎቻቸውን በተግባር እያሳዩ ውጤታማ ማስተማርን ታሳቢ በማድረግ ፍቃድ እንዲሰጥ የሚፈቅድ ረቂቅ ሕግ ተካቷል ነው ያሉት። በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ ኑሯቸው ነገር ግን ልምድ የሌላቸው በሁለተኛ ደረጃ የጥብቅና ፍቃድ እንዲሰጣቸውም የሚፈቅድ ረቂቅ አዋጅ ተካቶበታል፤ ይህም በወረዳ ደረጃ የሚደረጉ ክርክሮችን በጥብቅና መምራት የሚያስችል ነው ብለዋል ዶክተር ደሴ።

የጠበቆች ሥነ ምግባርን በተመለከተ አዳዲስ ዝርዝር ጉዳዮች ተካተዋል ያሉት ዶክተር ደሴ የጠበቆች ቦርድ እንዲቋቋም፣ የጠበቆች ማኅበር እንዲደራጅ፣ ጠበቆች ሥልጠና እንዲያገኙ የሚያግዝ አዳዲስ ድንጋጌዎች የታከሉበት ረቂቅ አዋጅ ነው ብለዋል። ረቂቅ አዋጁ የጥብቅና አበርክቶን የሚያጎላ መኾኑንም ዶክተር ደሴ አስገንዝበዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት የሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ ሃናን አብዱ በርካታ ማኅበረሰብ የሚገለገልበትን የጠበቆች አዋጅ ማሻሻል አስፈላጊ ኾኖ ተገኝቷል ብለዋል። ማኅበረሰቡ የጠበቃ አገልግሎት እንዴት ማግኘት እንደሚችል በረቂቅ አዋጁ ሰፍሯል፤ የዩኒቨርሲቲ መምህራን የጥብቅና አገልግሎት እንዲሰጡ የሚፈቅድ ረቂቅ አዋጅ ነው፤ ጠበቆች ምን ማድረግ እንዳለባቸውም በረቂቅ አዋጁ በዝርዝር ተካቷል ነው ያሉት።

የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ምክትል ኀላፊ አያሌው አባተ (ዶ.ር) ቀደም ሲል የነበረው የጥብቅና አገልግሎት፣ የጠበቆች ቁጥር፣ የደንበኞች አያያዝ፣ የኢኮኖሚ ደረጃ፣ የሕግ ጉዳዮች ውሥብሥብ ኾኖ ተገኝቷል ነው ያሉት። የጠበቆች የቁጥጥር ሥርዓት ውስንነት እንደነበረበትም አስረድተዋል። በመኾኑም አዋጁ እንዲሻሻል ረቂቁ አስፈልጓል ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ እና በዘላቂነት ለማቋቋም መንግሥት በትኩረት እየሠራ ነው” መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር)
Next articleከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የተማሪዎች መማሪያ ቁሳቁስ እና መጻሕፍት በጽንፈኞች ተቃጠለ።