“የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ እና በዘላቂነት ለማቋቋም መንግሥት በትኩረት እየሠራ ነው” መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር)

44

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ባለፉት ጊዚያት በተለያዩ ምክንያቶች ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ ጥረት እየተደረገ መኾኑን የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) ገልጸዋል፡፡ በተለይም ደብረ ብርሃን መጠለያ ጣቢያ ያሉ ተፈናቃዮች ቁጥራቸው በርክት ያሉ መኾኑን ያነሱት ቢሮ ኀላፊው፤ ከክልሉ ውጪ እና በክልሉ ውስጥ ተፈናቅለው ያሉ ዜጎችን ለመመለስ እየተሠራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ከኦሮሚያ ክልል የመጡ ዜጎችን ለመመለስ ከኦሮሚያ መንግሥት አመራሮች ጋር የክልላችን ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ተፈናቃይ ወገኖች ባሉበት ውይይት ተደርጎ እንዲመለሱ መደረጉን ያነሱት ኀላፊው በዘላቂነት ችግሩን ለመፍታትም ተደጋጋሚ ውይይት ተካሂዷል ነው ያሉት፡፡

ተፈናቃዮች ሲመለሱ ማኅባራዊ አግልግሎት የሚያገኙባቸውን ተቋማት በተለይ የሰላም እና የፀጥታ ኹኔታ፣ ውኃ፣ መብራት፣ መንገድ፣ የጤና ተቋማት ተገንብተው እና ሌሎችም እንዲሟሉላቸው ለማድረግ ጥረት ስለመደረጉ አንስተዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ያሉ የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች፣የሃይማኖት አባቶች፣ እና የመንግሥት አመራሮች ወጥተው እንዲቀበሏቸው ተደርጓል ብለዋል፡፡

ተፈናቃዮችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ የሁለቱ የክልል አመራሮች እና ሌሎች አካላት ድርሻቸው ከፍተኛ መኾኑን የገለጹት ኀላፊው ዜጎች ወደ ነበሩበት እንዳይመለሱ ለማድረግ የሚመሞክሩ የፖለቲካ ትርፍ ፈላጊዎች ነበሩ ነው ያሉት፡፡በዜጎቻችን ላይ የሚደረገውን ተገቢ ያልኾነ ተግባር ለማስቆም ከፍተኛ ዋጋ ተከፍሏል ነው ያሉት፡፡

ቀሪ መመለስ የሚገባቸው ዜጎች መኖራቸውን የጠቆሙት ኀላፊው በሁለቱም ክልሎች እየተሠራ ያለው ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። ከሁለቱ ክልሎች ጋር የሰላም ሚኒስቴር በጋራ ሥራዎችን ሲከውን መቆየቱንም ገልጸዋል፡፡ “በቀጣይም ዜጎችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ እና በዘላቂነት ለማቋቋም መንግሥት በትኩረት እየሠራ ነው” ብለዋል።

በቀጣይም ከቀሪ ተፈናቃይ ወገኖቻችን ጋር ተከታታይ ውይይት በማደርግ ችግሮቻቸውን መለየት እና መፍትሄ መስጠት አስፍላጊ ነው ያሉት ኀላፊው በተሳሳተ መንገድ የሚነሱ አስተሳሰቦችን ለማስተካከል በጋራ መታገል ይገባል ብለዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበጎንደር ከተማ የከተራ እና ጥምቀት በዓልን በሰላም ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው።
Next article“አዳዲስ ጉዳዮችን ለማካተት እንደ ክልል የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ አስፈልጓል”ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር)