ተስፋችንን አታጨልሙብን

33

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የሚገኙ ተማሪዎች በጸጥታ ችግር ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው ርቀዋል። ይህን ተከትሎም ለተለያዩ ችግሮች ተጋልጠዋል። ትምህርት ቤቶችም በጦርነቱ ምክኒያት መጎዳታቸው፣ መምህራን ላይ የተለያዩ ጫናዎች መድረሱ እና መሠል ችግሮችም አሳሳቢ ኾነዋል።

“ማን ይናገር የነበረ፤ ማን ያርዳ የቀበረ”ነውና ብሂሉ በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንደር በለሳ ወረዳ ጓኋላ ከተማ የምትኖረው የ16 ዓመቷ ታዳጊ ስለጉዳዩ ለአሚኮ ሃሳቧን ሰጥታለች። በ2015 የትምህርት ዘመን የ11ኛ ክፍል ተማሪ ነበረች። እንደ ክልል ያጋጠመው የጸጥታ ችግር ወላጅ አባቷን በሞት አሳጥቷታል።

የአባቷን ሞት ተከትሎም የእርሻ በሬዎቻቸው ቀንበር ፈቱ። ያ ባቄላ፣ ጤፍ እና ማሽላ ይመረትበት የነበረው የእርሻ መሬት ጦም አደረ። ህይወት ለእርሷ እና ለቤተሰቧ ፈታኝ ኾነ። በአካባቢው በገጠመው ግጭት ምክንያትም በበለሳ ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን ያስታዎሰችው ተማሪዋ ጦርነቱ ቤተሰባቸው ላይ ያሳረፈው በትር ድርብ ኾነ።

ወላጅ እናቷም የበኩር ልጃቸው ቤተሰቡ የገጠመውን ክፉ ቀን እንድታሳልፍላቸው ፈረዱባት እና ከሰው ቤት አስገቧት። ሌላው ባለታሪካችን በባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ በጭስ ዓባይ ዙሪያ የድንጋይ ደባሎ ቀበሌ ነዋሪ ነው። በሰላም እጦት ይማርበት የነበረው ትምህርት ቤት በመዘጋቱ አሁን ላይ የዘጠነኛ ክፍል ትምህርቱን አቋርጦ ከብት እየጠበቀ እና የእርሻ ሥራ እያከናወነ ይገኛል።

ጠንክሬ በመማር ሳይንቲስት የመኾን ራዕይ ነበረኝ የሚለው ይህ ተማሪ ግጭቱ ከልጅነት ሕልሙን እንዳያሳካ እንቅፋት እየኾነብኝ ነው አለን። ሌላዋ ባለታሪካችን በሰሜን ጎጃም ዞን የደቡብ አቸፈር ነዋሪ ናት። ባለታሪካችን በ2015 የትምህርት ዘመን የስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተናን በመውሰድ ጥሩ ውጤት በማምጣት ወደ ዘጠነኛ ክፍል አልፋለች።

“ሳይንቲስት”የመኾን ራዕይ አላት። ይሁን እና በአካባቢው የተከሰተው ግጭት ለመማር ጉጉ የኾኑ ተማሪዎችን ሕይዎት ተስፋ ማደብዘዙን ነው ተማሪዋ የምትናገረው። ግጭቱ ጠንክሮ ትምህርት ቤት እንደማይከፈት የተረዱት አክስቷ ወላጆቿን አስፈቅደው ወደ ባሕር ዳር ከተማ ወሰዷት። ጣና ሐይቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም ገባች።

በ2016 የትምህርት ዘመንም ጉብዝናዋን አስቀጥላ በመማር ከ53 ተማሪዎች ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ወደ 10ኛ ክፍል አለፈች። “በቅርቡ ወደ ትውልድ ቀዬዬ ደውየ ነበር” የምትለው ባለታሪካችን “ስለእነዚያ የትምህርት ቤት ጓደኞቼ ደስ የሚል ዜና አልሰማሁም። አንዷ የደብተር ቦርሣ በመያዥያ ጀርባዋ ልጅ ማዘሏን ሰምቻለሁ። ሌሎቹ እንዲኹ መማርን ቢሹም የሰላም እጦቱ ተስፋቸውን አጨልሞታል” ብላለች።

የኾነው ኾኖ ግጭቱ በሰላም ተፈትቶ የተማሪዎች የነገ ተስፋ ላይ የተጋረጠው ችግር እንዲቀረፍም ጠይቃለች። በሰሜን ጎጃም ዞን የይነሳ ሦሥቱ ቀበሌ ነዋሪ የኾኑት የተማሪ ወላጅ አሁን በአካባበቢያቸው አንጻራዊ ሰላም መኖሩን መስክረዋል። “መምህራንም ወደ ትምህርት ቤት እየመጡ ነው፤ ነገር ግን ወላጆች የልጆቻቸውን ጉልበት ለሰብል ሥብሠባ ስለሚፈልጉ ግጭቱን አሳበው ተማሪዎችን አስቀርተዋቸዋል” ብለዋል።

“እኔ በበኩሌ ለማስተማር ዝግጁ ነኝ። ሌሎችም ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት መላክ አለባቸው ነው ያሉት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleግጭት ያልፋል፣ ትውልድ ግን ይቀጥላል፤ ትውልድ ደግሞ የሚቀረጸው በትምህርት ነው።
Next articleበጎንደር ከተማ የከተራ እና ጥምቀት በዓልን በሰላም ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው።