
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ)መምህርነት ዕውቀት መስጠት፣ ትውልድን ቀርጾ ሀገርን ማሻገር ነው ተግባሩ። ይህንን ተግባር ማደናቀፍ ነገን አሻግሬ አያለሁ፣ ለትውልድም እጠቅማለሁ ከሚል ዜጋ ፈጽሞ የማይጠበቅ ነው። ይሁን እንጅ የትምህርት ቤት በሮች እንዲዘጉ፣ ተማሪዎች ከዕውቀት ገበታቸው ላይ እንዲነሱ፣ የዕውቀት ጠመኔ የጨበጡ የመምህራን እጆችም እንዲታጠፋ የሚፈልጉ መኖራቸውን ታዝበናል። ይህ ፍላጎት በተግባርም ተተርጉሞ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከጉዟቸው ተናጥበዋል።
በምሥራቅ ጎጃም ዞን እነማይ ወረዳን ለአብነት ብንወስድ 62 የመጀመሪያ ደረጃ እና አምስት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አሉት። ሥራ ላይ ያሉት ግን ስምንት የመጀመሪያ ደረጃ እና ሁለት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ናቸው። ከ67 ትምህርት ቤቶች ውስጥ 57ቱ ዝግ ናቸው ማለት ነው።
የእነዚህ ዝግ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የት እየዋሉ ይሆን? መምህራንስ እንዴት እያሳለፉ ይኾን? ተማሪዎችን፣ መምህራንን እና የትምህርት ዘርፍ ኀላፊዎችን አነጋግረናል።
ባለ ታሪካችን ታታሪው መምህር “የምሠራው ሥራ ለተሞክሮ የሚጠቅም ከኾነ እነግራችኋለሁ፤ ሥራየ እንዲደናቀፍብኝ ሥለማልፈልግ ሥሜን ግን አትጥቀሱት” ነው ያሉን በቃለ መጠይቃችን መግቢያ ላይ። ከዚህ በፊት በምሥራቅ ጎጃም ዞን እነማይ ወረዳ በገጠራማው ክፍል በሚገኝ ትምህርት ቤት ነበር የሚሠሩት። ዛሬ ያ ለተማሪዎቻቸው ዕውቀትን ይመግቡበት የነበረ ትምህርት ቤት ዝግ ነው። ተማሪዎች ከመምህራን ተለያይተው ተበትነዋል። በፊት በዕውቀት እና በምግባር ይኮተኩቷቸው የነበሩ ተማሪዎች የዛሬ መዋያቸው ምን እና የት እንደኾነ እንደማያውቁ፣ ግን እንደሚያስጨንቃቸው መምህሩ ነግረውናል።
እኒህ የዕውቀት አባት ያስተምሩበት የነበረው ትምህርት ቤት በታጣቂዎች ግፊት ይዘጋ እንጅ እርሳቸው ግን ባገኙት ሁሉ አጋጣሚ ዕውቀታቸውን ከመስጠት አልቦዘኑም።
“የተበተኑ የሰፈር ልጆችን ከየመንደሩ ሰብስቤ አስተምር ነበር” ይላሉ። ይህም ተማሪዎች አልባሌ ቦታ ከመዋል ይልቅ ሰብሰብ ብለው ዕውቀት እንዲያገኙ ያደርጋል፣ በሥነ ልቦናም ይደግፋቸዋል ነው ያሉን መምህሩ። አሁን ላይ በእነማይ ወረዳ ሰላም ሰፍኖ ትምህርት ወደተጀመረባቸው አካባቢዎች ተዛውረው በተለይም ብሔራዊ ፈተና ለሚወስዱ ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት ጊዜያቸውን እያሳለፉ ነው። “በቋሚነት የተመደብኩበት ትምህርት ቤት ተከፍቶ መደበኛ ሥራ እንዲጀመር ብርቱ ፍላጎት ነበረኝ፤ ግን አልኾነም” ሲሉ ይናገራሉ።
ትምህርት ቤታቸው እስከሚከፈት እጃቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም። ወደ ቢቸና ከተማ በመምጣት እና ከትምህርት አመራሮች ጋርም በመነጋገር ተማሪዎችን በተቃራኒ ፈረቃ እያስተማሩ፤ ለተሻለ ውጤት እና ሀገራዊ ተወዳዳሪነት እያዘጋጁ ነው። “ነገ ለሚያልፍ ችግር የሀገር ተረካቢ ልጆቻችንን ህልም በከንቱ ማለፍ የለበትም፣ ትምህርት እና ትምህርት ቤቶችን ከምንም ነገር ነጻ አድርጎ ማሰብ ግድ ይላል” ሲሉም አሳስበዋል መምህሩ።
በየአካባቢው ትምህርት ቤቶቻቸው የተዘጉባቸው መምህራን አሉ፤ ዕውቀት ከመስጠት መራቅ የለባቸውም፣ በጊዜያዊነት ወደ ሌሎች አካባቢዎች እየተዘዋወሩ በተለይም ዘግይተው ትምህርት የጀመሩ ተማሪዎችን በማገዝ ማብቃት አለባቸው ሲሉም መክረዋል።
የአካባቢው ተማሪዎችስ ምን ይላሉ?
ስሙን መጥቀስ ያልፈለገ አንድ ተማሪ ከወረዳው ገጠራማ ቀበሌ ወደ ቢቸና በመምጣት ለአንድ ዓመት ያቋረጠውን ትምህርት ጀምሯል። በትውልድ ቀየው የሚገኘው ትምህርት ቤት በመዘጋቱ ከወላጆቹ ጋር ኾኖ መማር የሚችለውን ትምህርት በቢቸና ከተማ በጫና ውስጥ ኾኖ እንዲማር ተገድዷል።
የቤት ኪራይ እና ሌሎችም ወጭዎች እና ሁኔታዎች ተደማምረው ፈተና እንደኾኑበትም ገልጿል።
በተለይም ደግሞ ለትምህርት ብሎ ከቀየው መውጣቱን የሰሙ ታጣቂዎች ቤተሰቦቹን በመያዝ የገንዘብ ቅጣት እንደጣሉባቸው ሲናገር “ከፍተኛ በደል ነው” ብሎናል። በዚህ ጫና ውስጥ ኾኖ ትምህርቱን መቀጠል እንደሚከብደው እና አቋርጦት ወደ ቤተሰቦቹ ለመመለስ እንደሚገደድም ስጋት እና ጭንቀቱን ገልጿል።
“ሀገር ለመቀየር ከኾነ እንማር” የሚለው ይህ ተማሪ ሰላም ሰፍኖ በትውልድ ቀየው የሚገኘው ትምህርት ቤት እንዲከፈትለትም ጠይቋል። ትምህርቱን ዘግይቶ እንደ ጀመረ ገልጾ፣ ለብሔራዊ ፈተናዎች ዝግጁ እንዲኾኑ መምህራን ለሚያደርጉላቸው ድጋፍ አመስግኗል። በሚማርበት ቢቸና ከተማ በተቃራኒ ፈረቃ እሁድ እና ቅዳሜን ጨምሮ እየተማርን ነው፤ ቤተ መጽሐፍትም ሁሌም ክፍት ነው ብሏል።
የእነማይ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ግዛቸው ምኑየ እንዳሉት የጸጥታ ችግሩ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ አደጋ ደቅኗል። የተማሪዎችን የመማር መብት አሳጥቷል። አካባቢዎች ሰላም በኾኑ ጊዜ ሁሉ ተማሪዎችን በመመዝገብ ወደ ትምህርት ቤት እየመለሱ እንደኾነም ገልጸዋል። ዘግይተው የመጡ ተማሪዎች ያለፋቸው ትምህርት እንዲካካስ፣ ተወዳዳሪም እንዲኾኑ የሚያስችል አሠራር ስለ መዘርጋቱም አብራርተዋል።
ትምህርት ባልተጀመረባቸው ትምህርት ቤቶች ይሠሩ የነበሩ መምህራን ትምህርት በጀመሩ ትምህርት ቤቶች ተመድበው እያገዙ ነውም ብለዋል። በትምህርት ዝግጅታቸው፣ በሥራ ትጋታቸው እና በማስተማር ክህሎታቸው የተሻሉ መምህራን ተመርጠው ብሔራዊ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎችን የማብቃት ሥራ እያከናወኑ ስለመኾኑም ጠቅሰዋል።
ከመደበኛው ትምህርት በተጨማሪ የሥነ ልቦና ድጋፍ ጭምር ለተማሪዎች እየተሰጠ ስለ መኾኑም ተናግረዋል ኀላፊው። “ግጭት ያልፋል፣ ትውልድ ይቀጥላል፣ ትምህርት ትውልድን የመቅረጽ ተግባር ነው፤ ማንም ቢኾን ይህንን ተረድቶ ትምህርት ቤቶች ክፍት ኾነው ሥራቸውን እንዲያከናውኑ መደገፍ አለበት” ባይ ናቸው ጽሕፈት ቤት ኀላፊው።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የኅዝብ ግንኙነት ኀላፊ ጌታቸው ቢያዝን እንዳሉት መደበኛውን የትምህርት ጊዜ ጠብቀው መመዝገብ ላልቻሉ ተማሪዎች ሁለተኛ ዙር የምዝገባ ቀናት ተመቻችተዋል። ሁለተኛው ዙር ምዝገባ ከኅዳር 15 ጀምሮ እየተካሄደ ሲኾን እስከ ታኅሣሥ 21/2017 ዓ.ም የሚቀጥል ይኾናል።
ይህ የምዝገባ ቀን ተወስኖ የተቀመጠ ቢኾንም በአካባቢያቸው ሰላም የሚከፈቱ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን በመመዝገብ ማስተማር እንደሚችሉም ኀላፊው ገልጸዋል። አቶ ጌታቸው እንዳሉት ቢሮው ዘግይተው ወደ ትምህርት ቤት የመጡ ተማሪዎችን የማብቃት አሠራር ዘርግቷል። አዲስ የተመዘገቡ ተማሪዎች ለብቻ ተለይተው የማካካሻ ትምህርት ይሰጣቸዋል፤ እሁድ እና ቅዳሜ እንደ መደበኛ የትምህርት ቀን ኾነው ያገለግላሉ፤ የትምህርት ቤቶች ነባራዊ ኹኔታ እየታየ በተቃራኒ ፈረቃ እና በምሽትም የንባብ እና የትምህርት ጊዜ ይመቻቻል ነው ያሉት።
መደበኛውን የትምህርት ይዘት በአጭር ጊዜ ለመሸፈን የሚያስችል የትምህርት ክፍለ ጊዜ ቢሮው አዘጋጅቶ ለየ ትምህርት ቤቶች በተዋረድ ስለ መሰራጨቱም ተናግረዋል። አቶ ጌታቸው ተማሪዎች ጠንካራ አላማ ይዘው ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ፣ መምህራንም ተማሪዎችን እየተቀበሉ ለማብቃት እንዲታትሩ፣ በተዋረድ ያሉ የትምህርት አመራሮችም ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርጉም አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!