ሰላምን ለማረጋገጥ እንደሚሠሩ በዳባት ከተማ የተሐድሶ ሥልጠና እየወሰዱ የሚገኙ ሠልጣኞች ተናገሩ።

46

ጎንደር: ታኅሣሥ 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) መንግሥት የሀገርን ሰላም ለማጽናት በአማራ ክልል ታጥቀው ወደ ጫካ የገቡ አካላት ወደ ሰላም እንዲመጡ የሰላም ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል። የመንግሥትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ ታጣቂዎች በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች የተሐድሶ ሥልጠና እየወሰዱ ነው።
በሰሜን ጎንደር ዞን በዳባት ከተማ አሥተዳደር የተሐድሶ ሥልጠና ሲወስዱ አሚኮ ያነጋገራቸው ሠልጣኞች “ያለ ሰላም ሕይዎት ባለመኖሩ ስለ ሰላም እንተጋለን”ብለዋል።

ሠልጣኞቹ “ተማሪዎች ትምህርታቸውን ማቋረጣቸው፤ እናቶች ወደ ጤና ጣቢያ መድረስ ባለመቻላቸው፣ የሰላም እጦት በማኅበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ እንደሚገኝ በመገንዘባችን የሰላም ጥሪውን በመቀበል ለሕዝቡ ሰላም ለመስጠት የተሐድሶ ሥልጠና እየወሰድን ነው” ብለዋል። ሠልጣኞቹ በሥልጠናው ደስተኛ መኾናቸውንም ተናግረዋል። ትጥቅ ይዘው የሚታገሉ አካላት ወደ ሰላም እንዲመጡ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡም ገልጸዋል።

በዳባት ከተማ አሥተዳደር ማሠልጠኛ ማዕከል ከ900 በላይ የመንግሥት የሰላም ጥሪ የተቀበሉ ታጣቂ ኀይሎች የተሐድሶ ሥልጠና እየወሰዱ መኾኑን የሥልጠናው አስተባባሪ ፋሲል ድልነሳ ገልጸዋል። አስተባባሪው በክልሉ እና በሀገር አቀፍ ወቅታዊ ሁኔታ እና በሰላም እሴት ግንባታ ዙሪያ የአቅም ግንባታ ሥልጠና እየተሰጠ መኾኑን ነው የተናገሩት።

ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት ነው ያሉት አቶ ፋሲል ሠልጣኞች ከሥልጠናው ያገኙትን ዕውቀት እና ልምድ በመጠቀም ወደ ማኅበረሰቡ ሲቀላቀሉ ስለ ሰላም ሊያስተምሩ ይገባል ነው ያሉት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleተፈናቃዮችን በዛላቂነት ለማቋቋም ኹሉም አካል ርብርብ እንዲያደርግ ተጠየቀ።
Next articleፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ መቄዶንያ የአረጋውያን እና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከልን ጎበኙ።